በረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል

እንደ መግቢያ

አሰላሙ አለይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካቱ የአል-ኢስላም መፅሄት ዝግጅት ክፍል አዘጋጆች እና የተከበራችሁ የመፅሄቷ አንባቢያን ….. ቀደም ሲል በዚሁ አምድ ላይ “አህባሾችና ስዉር አጀንዳዎቻቸዉ” በሚል ርዕስ የተፃፈዉን ፊቸር አንብቤዋለሁ። ፅሁፉ ከሞላ ጎደል በበቂ ደረጃ የአህባሽን ቡድን ታሪካዊ መሰረት ቁልጭ አድርጎ ከመረጃዎች ጋር በማስደገፍ በማቅረቡ ዛሬ ስለ አህባሽ ምንነት ተጨማሪ ማብራሪያ ለመፃፍ ብዕሬን አላነሳሁም። በኢስላማዊ ፕሬሶቻችን እስካሁን ያልተዳሰሰዉን አጀንዳ በማንሳት ለአንባቢያን በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በመፈለግ እንጂ!

ይኼዉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምናልባትም ከአምስት ወራት ወዲህ በአገራችንም ሆነ ከአገር ዉጪ የሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያንን እያነጋገረ የሚገኘዉ የአህባሽ ቡድን በአሁኑ ወቅት የሚያደርገዉና እያደረገ ያለዉ እንቅስቃሴ አገራዊና አለምአቀፋዊ አንድምታዎች ምን ገጽታዎች እንዳላቸው መመልከቱ አስፈላጊ መሆኑን በማመኔ ነዉ። ይህን ሀሳብ ለማብራራት ወቅታዊና ነባራዊ መረጃዎችን እያጣቀስኩ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ጉዳይ ቀደም ሲል በመፅሄቷ አጀንዳችን አምድ የሰፈረዉን ፅሁፍ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ትርጉም እና አንድምታዉን ባለመተንተኑ ሲሆን ፤ይህ መሰረታዊ ጉዳይ የብዙዎቻችን ሙስሊሞች ጥያቄ እንደሚሆን በማመን ያለኝን ዕዉቀት ወይም መረጃ የማካፈል ህዝባዊ ሀላፊነት በመጠኑም ቢሆን ለመወጣት ጭምር መሆኑን ተረዱኝ።

በተጨማሪም ይህን ፅሁፍ የሚያነቡ የአል-ኢስላም አጀንዳችን አምድ አንባቢያን እንዲገነዘቡልኝ የምፈልገዉ ነጥብ በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መድረኮች በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅለይ ምክር ቤት አስፈፃሚነት እና በኢፌድሪ መንግስት በተለይም በፌደራል ጉዳዩች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተባባሪነት ከሊባኖስ በመጡ የአህባሽ ቡድን መሪዎች አማካኝነት እየተሰጠ የሚገኘዉን ስልጠና ተከትሎ በአገራችን ሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ የአመለካከት እና የእምነት መከፋፈል ሳይሆን የእርስ በርስ ወንድማማችነትና አንድነት እንዲጠናከር ከማድረግ አንፃር የቡድኑን ወቅታዊ እንቅስቃሴ ከዓለም አቀፋዊ ክስተቶችና ከተጨባጭ አገራዊ ሁኔታዎቻችን ጋር እያገናዘቡ መመልከት ጠቀሜታዉ የጎላ መሆኑን በማመን ካለኝ የንባብ እና የጥናት ምርምር ሥራዎቼ መረጃዎችን በማጣቀስ ፅሁፉን ላዘጋጅ የመቻሌን ጉዳይ ነዉ ። ከዚሁ ጋር በተለይ በስልጠናዉ ሂደት መጅሊስን ወይም መንግስትን ለመክሰስ ሳይሆን ለማስገንዘብ፣ ለመዉቀስ ሳይሆን ለመማማር፣ለመተቸት ሳይሆን መረጃ ለመስጠት ወይም ለመለዋወጥ ይጠቅማል ከሚል ቀና አመለካከት ተነስቼ እንደፃፍኩ ለመጠቆም እወዳለሁ። ከዚህም በላይ በቡድን አመለካከቶች እየተምታታ የሚገኘዉ ሰፊዉ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ስለ ቡድኑ እና ወቅታዊ እንቅስቃሴዎቹ አስፈላጊነት ዙሪያ የመረጃ ጥማቱን በመጠኑም ቢሆን ለማስታገስ ይህ ፅሁፍ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ከሚል እሳቤ ተነስቼ መፃፌን ማስረዳት ተገቢ ይመስለኛል።

ወደ ርዕሰ ጉዳዩ ልመለስና በዚህ ወቅት የአህባሽ ቡድን በአገራችን አመለካቱና እምነቱን ለማስረፅ እንዴት ፈለገ ? ወይም የአህባሽ አመለካከት በኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለምን ተፈለገ ? ለሚለዉ የብዙሃኑ  ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ልሞክር… ከዓለም አቀፋዊ ነባራዊና ወቅታዊ ክስተቶች አንፃር የአህባሽ ቡድን የሚኖረዉን አንድምታ በመተንተን ልጀምር ……

የቡድኑ አመለካከት እና ዓለም አቀፋዊ ገፅታዎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሶሻሊስት ርዕዮተ አለም አመለካከት ከፈራረሰ በኋላ በተለይም በምንገኝበት ዘመን የዓለም ማህበረሰብ በግሎባላይዜሽን ጥላ ስር እንዲሰባሰብ ብሎም የአንድ ባህል ፤ወግና ልምድ አራማጅ እንዲሆን ወይም በአንድ ማህበረሰባዊ ኢኮኖሚ (social economy) ሥርአት እንዲመራ የሚለዉ የፖለቲከኞች አመለካከት የበላይነቱን ይዞ ይገኛል። በሆላንድ ዋና ከተማ ሄልሲንኪ በተካሄደዉ ስብሰባ እነማርክ ዴክፓርቸርና እነ ኒክሰንን ጨምሮ ሌሎችም ታላላቅ የፖለቲካ ሊቃዉንት አማካኝነት የተነደፈዉ ይህ ዕቅድም ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል ።ይሁንና ዕቅዱን ለማሳካት ከፊትለፊት ያለዉ አስቸጋሪው ፈተና ከእስልምና ሃይማኖት መስፋፋትና መጠናከር ጋር የተያያዘ አድርገዉ ይመለከቱታል። ከ15 ዓመታት በኋላ እንደ ሶሻሊስት በቀላሉ የሚመታ ሃይመኖት አለመሆኑን የተገነዘቡት እነዚሁ ምዕራባዊያን ፖለቲከኞች ታዲያ ሀይማኖቱ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚከፋፈልበትን ስትራቴጂክ ስልት የመጠቀም ዘመቻቸዉን በሰፊው እያካሄዱ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት የሀይማኖቱን ዓለም አቀፋዊ አንድነት ለማዳከም እየጣሩ ያሉት፤ በዓለም አቀፋዊ ደረጃ በተለያዩ ክፍለ አህጉራት እየተከሰቱ ያሉት ፖለቲካዊ ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጠዉ የእስልምና ሀይማኖት አስተምሮቶች መሆናቸዉን በጊዜ ሂደት እየተገነዘቡ በመምጣታቸው ነዉ። ከምዕራባዉያኑ መካከል ጥቂት የማይባሉት ምሁራን ፣የፖለቲካና የተለያዩ አይዶሎጂዎችን እያራመዱ የሚገኙት እነዚሁ ወገኖች ይህንኑ እየተገነዘቡ ከመምጣታቸዉም በላይ እስልምና ለአለም ህዝቦች ሁሉ ተስማሚ ሀይማኖት መሆኑን በተለያዩ መንገዶች ማረጋገጣቸዉ ለፀረ ኢስላም ተዋናያኑና የፖለቲካ ሰዎች ትልቅ ራስ ምታት ሆኗል። በተለይ ደግሞ ለእስራኤላዉያኑ!

የዓረቡን ዓለም ክስተት ተከትሎ ያለው ስጋት

በመካከለኛዉ ምስራቅ ካለፉት አስር ወራት ወዲህ ያገረሸዉ ህዝባዊ አመፅ እስራኤላውያኑን እረፍት ነስቷቸዋል። በተለይም የመካከለኛዉ ምስራቅ አረብ ሀገራት ህዝቦች በመሪዎቻቸዉ ላይ ያላቸዉ አመኔታ እየመነመነ መምጣቱ እና ይህንንም ተከታሎም ለእስራኤል ታማኝ የሚባሉ መሪዎቻቸዉ ከስልጣናቸዉ እየወረዱ በመሆኑ እስልምናን ለማተራመስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗቸዋል። ይህ የቀጠናዉ አገራት የለዉጥና የነዉጥ ማዕበል ለእስራኤላውያን በጣም አስጊ ሆኖ ይታያል ። በአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴርም ሆነ በሌሎች አማካሪዎች እስራኤላውያን የራሳቸዉን ቤት እንደገና እንደ አዲስ ዕቅድ ነድፈዉ እንዲሰሩ ባሳሰቧቸዉ መሰረት የእስራኤል መሪዎች ወደ ፊት ከዓረቡ አለም ህዝቦች ጋር ስምምነትና ድርድሮችን ማድረግ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጥራል የሚል ስጋት አይሎባቸዉ ይታያሉ። በዚህም ከፍተኛ ዉጥረትና ጭንቀት ነግሶባቸዋል።

ኢትዮጵያም የስጋታቸዉ አካል ትሆን?

እስራኤሎች ኢትዮጵያን ከዐረቡ ዐለም ጋር ባላት ታሪካዊ ትስስር አንፃርም ሆነ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ ስትራቴጂያዊነት ሳቢያ ከዐረቡ ዓለም አገራት ለይተዉ አይመለከቷትም። በተጨማሪም በርካታ ህዝብ ቁጥር ያለዉ ኢትዮጵያዊ የእስልምና ሓይማኖት ተከታይ በመሆኑ ከአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች በግንባር ቀደምነት ራስ ምታት የሆነችባቸዉ ይመስላል። ስለሆነም እስራኤል የዐረቡ ዓለም የለዉጥና የነዉጥ ማዕበል ወደ ኢትዮጵያ እንዳይደርስ ያላትን ፍላጎት ለማንፀባረቅ ስትል ከተጠቀመችባቸዉ ስትራቴጂክ ዕቅድ አንዱና ዋነኛዉ የአህባሽ ቡድንን አመለካከትና አስተምሮት በኢትዮጵያዉያኑ ሙስሊሞች ላይ የማስረፅ ዘመቻዋ ነዉ። ምክንያቱም የአህባሽ አመለካከት ከእስራኤላዉያን አመለካከት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነዉና!።

ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ፣ ቲዉተር…የስጋት አካል ሆነዋል

ዓለምን ወደ መንደርነት ያቀራረበው የዘመናችን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስርፀት ህዝብን ለአንድ አላማ ለማሰለፍ አመቺ ሆኗል። እናም እንደ ፌስቡክ እና ቲዉተር የመሳሰሉ የመልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴዎች ለእስራኤላዉያኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስጋት መሆናቸዉ አልቀረም። ለምሳሌ እ.ኤ.አ ኦክተበር 15/2011 ብቻ ከስፔን፣ ስኮትላንድ ፣ጣልያንና አሜሪካን የዘለቀዉ ህዝባዊ ሰልፍ በ82 አገሮች 1 ሺ ከተሞች የሚኖሩ ህዝቦች ሃይማኖት፣ ዘር፣ ብሄርና ጎሳ ሳይለያቸዉ ለአንድ ዓላማ  ወደ አደባባይ እንዲወጡ ለማድረግ እነዚሁ የመልዕክት ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ማስታወስ ይቻላል። እነዚህን ህዝቦች መቀስቀስ የተቻለዉ በዘመኑ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፍሬዎች መሆኑ ታዲያ ለእስራኤላዉያን ተዘዋዋሪ የስጋት ደዉል እንዲያቃጭልባቸዉ ምክኒያት ሆኗል። በተጨማሪም የሙስሊሙና ዐረቡ ዓለም ሕዝባዊ ንቅናቄ በእነዚህ የቴክኖሎጂ ዉጤቶች ጭምር የታገዘ መሆኑ ታዲያ ለእስራኤል ዘመን ያልሻረዉና የማይሽረዉ ስጋት አከናንቧታል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት በዓለም ሃያላን አገራት ጭምር ለተከሰተዉ የኢኮኖሚ ቀዉስ እስልምና እንደ መፍትሄ እየተወሰደ መምጣቱ ለእስራኤላዉያንና ፀረ-ኢስላም እይታ ባላቸዉ ምዕራባዉያን የሙስሊምን ህዝብ እምነትና አመለካከት አቅጣጫ ለማስቀየር መባዘናቸዉን ተያይዘዉታል ።አጀንዳ ይዘዉና ዕቅድ ነድፈዉ ከሚንቀሳቀሱባቸዉ አቅጣጫ የማሳቻ ዘዴዎቻቸው መካከል ደግሞ ዋነኛዉ ስልት የአህባሽ ቡድንን አመለካከት የማስረፅ ሂደት ነዉ ።ይህ ነባራዊና ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ናቸዉ እንግዲህ የአህባሽ ቡድን እንቅስቃሴ በአገራችን ጭምር ተጠናክሮ እንዲመጣ ምክንያት የሆነዉ ። የዚህ ቡድን በአገር ዉስጥ እንዲስተናገድ ምክኒያት የሆኑትን ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታዎች ደግሞ በመቀጠል ለመጥቀስ እሞክራለሁ።

አገር አቀፍ አንድምታዎች

የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች በአፄዎቹ ዘመን በተለይ “በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙሰሊሞች” እየተባሉ ይጠሩበት በነበረበት ወቅት ከሀገራዊ የልማት እና የፖለቲካ አጀንዳዎች ተገልለዉ ኖረዋል። ከወታደራዊና ደህንነት ቦታዎች ርቀዋል። የመሪነት ሚና አልነበራቸዉም። ከዚህም በላይ የትምህርት ተሳትፏቸዉ እጅግ የመነመነ ከመባል ይልቅ ያልነበረ በሚባልበት ደረጃ ላይ ሆኖ ዘመናትን አሳልፈዋል። ባህልና እምነታቸዉን እየገበሩ የኖሩበት ያ ክፉ ዘመን  ዛሬ ላይ የለም። በህዝቦች የአመታት ትግል ሁሉንም የአገሪቱን ዜጎች የሀይማኖት ተከታዮች በእኩልነት ደረጃ እና በጋራ የሚያስተናግድ ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ዕዉን ሆኗልና! ይህንኑ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ተከትሎ በተፈጠረዉ ምቹ ሁኔታ ኢትዮጲያዊነታቸዉ ተረጋግጦ የፌዴራሊዝም ሥርአቱ ተዋናይና ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል። ከክልል እስከ ፌዴራል መንግስት ባሉ መዋቅሮች እንደሌሎች እምነት ተከታዮች ሁሉ የልማት እና ፖለቲካ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ መጥተዋል ።

ይሁንና ይህ የሙስሊሞች የተነቃቃ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ያልተዋጠላለቸዉ አንዳንድ የዉጭና የዉስጥ ሃይሎች ዛሬም ድረስ ለመኖራቸዉ አስረጂ መጥቀስ አያሻም። እነዚህ ሃይሎች ኢትዮጵያዊው ሙስሊም መማሩ፣ በልማት የመሳተፉ፣ ፖለቲካዊ ስልጣን መያዙ፣ በመንግስት የአስተዳደር የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር መገኘቱ…ወዘተ ይከነክናቸዋል። ስሙን፣ ባህሉን፣ ወጉን፣ ልምዱን፣ ቅርሱን፣ መንፈሳዊና አገራዊ ማንነቱን እንዳይዝ፤ እዚህም እዚያም የሚያደርገዉ ሀገራዊ ተሳትፎ በእርግጥም ጥቂት የማይባሉትን የዉጪና የዉስጥ ሃይሎችን አሳስቧል። አስጨንቋልም! ይህንኑም ጭንቀት ለማርገብ የተያዘዉ አንዱ አማራጭ የተረጋጋና ሠላማዊ የኢትዮጲያ ሙስሊሞች ማህበረሰብ አንድነቱን ጠብቆ እንዳይቀጥልና እንዳይጠናከር የቤት ስራ መስጠት ነው። ለዚህ ደግሞ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአገራችን እየተስተናገደ ያለዉ የአህባሽ ቡድን እንቅስቃሴ በቂ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ነዉም!!

አንዳንድ የዉጭና የዉስጥ ፀረ-ኢስላም ሃይሎች ያሳሰበዉ ጉዳይ የሙስሊሙ የተነቃቃ ተሳትፎ ብቻም አይደለም፤ በትክክለኛዉና በቅርቡ በተደረገዉ የቤቶችና ህዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት የህዝበ ሙስሊሙ ቁጥር ከጠበቁት በላይ ገዝፎ የመዉጣቱ ጉዳይም ሌላዉ ጭንቀታቸዉ ሆኖ ይታያል።  ከዚህ ፈጣን የህዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር በተያያዘ ይህ ሙሰሊም ማህበረሰብ አንድነቱን ጠብቆ ከዘለቀና አሁን ካለዉ መንግስታዊ ስረዓት ጋር ተቀራርቦ ለሃገሩ ልማት ከሰራ ውሎ አድሮ ሠላም የሚነሳቸዉ ሃይሎች አይታጡም። ለአብነት ያህል በ1997ና በ2002 በተካሄዱት አገር አቀፍ ምርጫዎች ብዙሃኑ የአገሪቱ ሙስሊም ማህበረሰብ ኢህአዴግን በድምጹ መርጦኣል። ሙስሊሙ እንደ ትላንቱ ሁሉ ወደፊትም ለኢህአዴግ ድምጹን መስጥቱን ከቀጠለና አጋርነቱን ካረጋገጠ የእነዚህ እኩይ ሃይሎች ስጋት እጥፍ ድርብ መሆኑ አይቀሬ በመሆኑ ከወዲሁ በተለይም ከሶስት ዓመት በኋላ የሚካሄደው አምስተኛዉ ዙር ብሄራዊ ምርጫ ከመድረሱ አስቀድሞ መንግስትን ከህዝበ ሙስሊሙ ጋር ለማጋጨት ወይም ለማራራቅ የሚረዱ ስራዎችን ለመስራት ቀን ከሌት እየደከሙ ይገኛሉ ። በቀጣዩ ምርጫ ሙስሊሙ ለኢህአዴግ ድምፅ የሚሰጥበትን ዕድል ለማኮላሸት የሚደረግ ፅኑ እንቅስቃሴ መታየት በቂ ማስረጃ ሆኖም ይታያል ። እናም “አህባሽ ” የሚለዉ እምነት እና አመለካከት በኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ላይ ለማንሰራፋት የተጀመረዉ ዘመቻ ከላይ በተጠቀሱትና በግልፅ ባልተነገሩት ስዉር አጀንዳ አራማጆች ግፊትና ጫና ምክንያት ስለመመንጨቱ  መገንዘብ አያዳጋትም።

ህዝበ ሙስሊሙን ከመንግስት ጋር ያለዉን መልካም ግንኙነት ለማበላሸት እና ሙስሊሙ መንግስትን ፤ መንግስት ደግሞ ብዙሃኑን ሙስሊም እንዲሸሸ የሚያደርጉ የዉጪና የዉስጥ ሃይሎች መኖራቸዉን ዘንግተዉ የአህባሽን እንቅስቃሴ የሚያስተናግዱና በተለይም እየተሳተፉና ድጋፍ እየሰጡ ያሉ ጥቂት የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ሊከተል የሚችለዉን አሉታዊ ችግር ተገንዝበዉ ይሆን? ወይስ ያሳሳታቸዉና እያሳሳታቸዉ የሚገኝዉን ሃይል በማወቅም ሆነ ብለማወቅ አልተገነዘቡም? የሆነ ሆኖ እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ቆም ብሎ እጅግ በሰከነ መንፈስ ማስተዋልና መፈተሹ ተገቢም ወቅታዊም ይመስላል።

እንደ መሸጋገሪያ

አህባሾች ከእስራኤል ጋር ያላቸዉ ግንኙነት ቀደም ሲል “አህባሾች እና ስዉር አጀንዳዎቻቸዉ” ፅሁፍ ላይ ያልተጠቀሰዉ የቡድኑ መስራች አብደላ አል ሃረሪ ቀደም ሲል ሊባኖስ ከመሄዱ በፊት በሃረር በፈጠረዉ ዉዝግብ በርካታ ኡለሞች ከሃገር እንዲወጡ ያደረገዉ ከአፄ ሃይለስላሴ ገዢ መደብ ጋር በመመሳጠር እነደነበር ነዉ። በኡለሞች ላይ ያደረሰዉ አሰቃቂ ግፍ እና በደል ዓይነቱ ብዙ ነበር ። እርሱ ያስከተለዉ የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑ ዑለሞች ዛሬም ድረስ እዚሁ በአገራችን በህይወት አሉና ዝርዝሩን እነርሱ እንዲናገሩ እንተዉላቸዉ። ከአይሁድ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ትንሽ ነገር ለማለት ያህል፤ አብደላ አልሃሪሪ በግብፅ፣ በሶሪያና በእስራኤል ባደረገዉ እንቅስቃሴ ተልዕኮዉን ለመፈፀም አመቺ መድረክ አላገኘም ነበር ። በወቅቱ የ17 ዓመት ጦርነትን ያስተናገደችዉ ሊባኖስ ግን ዋነኛ መድረክ ሆነዋለች። በወቅቱ ሊባኖስ የብዙ ጎሳዎች መኖሪያና በእርስ በርስ ጦርነት የደቀቀች አገር ከመሆኗም በላይ እንደ ሺዓ፣ ሱንይ፣ ዴርዚነና እና ሌሎችም አመለካከቶችን የሚያራምዱ ህዝቦችን በግጭት ስታስታምም የኖረች ሃገር ነች ። በአሁኑ ወቅትም ይህ ሁኔታ በጠራ ሁኔታ ላይ አለመገኘቱ እንዳለ ሆኖ አንድም ጊዜ ሠላምና መረጋጋት ያልታየበት ሆና ቆይታለች። የሊባኖስ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሱንይ ነበር ። የፓርላማዉ አፈ ጉባኤ ሺአ የነበረ ሲሆን፤ ፕሬዘዳንቱ ደግሞ ክርስቲያን ሆኖ እናገኘዋለን … የሆነ ሆኖ አብደላ አልሃሪሪ እንቁላሉን እንዲህ ዓይነት ታሪካዊ ስዕል በነበራትና ባላት ሊባኖስ ነው የጣለው፡፡ በወቅቱ በአመለካከቱ ያጠመቃቸውን የፓርላማ አባላት እስከ ማፍራትም ደርሷል፡፡ በነገራችን ላይ አብደላህ አልሃራሪ እ.ኤ.አ. በ1982 በሊባኖስና በእስራኤሎች መካከል በተካሄደው ጦርነት ከሞሳድ ጋር በመተባበር የመረጃ ምንጭ ሆኖ ለእስራኤሎች ሲያገለግል የነበረ ነው፡፡ ይህ እስራኤል ጋር ምን ያህል የጠበቀ ቁርኝነት እንዳለው አመላካች ነው፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት በሰጠው ብይን (ኢፍታዕ) ነብዩ መሐመድ (ሠ.ዐ.ወ.) ከመካ መዲና የሸሹት አቅሙና መሰባሰቡ ያለው ሰራዊት ስላለነበራቸውና ሰራዊቱ ደካማ ስለለበር እንዲሆነ ፣ ስደቱን ያካሄዱት ለእምነታቸው ሲሉ መሆኑን በማብራራት ፍልስጤሞች ከጋዛም ይሁን ከሌላ ጋር ሆነው እስራኤልን በመልቀቅ ወደ ሌሎች ኢስላማዊ አገራት መስደድ እንዳለባቸው ሲናገር… በብዙሃኑ እስራኤላውያን ዘንድ ከፍተኛ የሆነ አድናቆትን አግኝቷል፡፡ ከዚህ ዝና መቸር ባለፈም ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ እስራኤሎች ታዲያ ዛሬም ድረስ የአህባሽ አመለካከትና አስተሳሰብ እንዲስፋፋ እየሰሩ የሚገኙት በዚሁ ምክንያት መሆኑን መገንዘብና ማስተንተን ጠቃሚ ነው፡፡

ከሊባኖስ የመጡ አስተማሪዎች እንዴት ይታመናሉ?

የአህባሽን አመለካከት ለማስረፅ ሲባል ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሊባኖሳዊያን መምህራን እንዴት ይታመናሉ ያልኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ሊባኖሳውያን በባህሪያቸው እንደመምህር ወይም እንደ መልካም ምሳሌ ተደርገው ስለማይወሰዱ እንጂ! እነዚህ ዜጎች ለኢትዮዽያውያን እንደማይበጁ የአደባባይ ሚስጥር ነው! ጥሩ ምሳሌ ልጥቀስ… ወደአገራቸው ለሥራ የሄዱ ኢትጵያውያን ላይ እየፈፀሙት ያለውና ለዘመናት ሲፈፅሙባቸው የኖሩት በደልና ስቃይ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡ ለሀበሻ (ለኢትዮጵያውያን) ያላቸው ሰብዓዊ ክብርና ደረጃ የዘቀጠ መሆኑን በቅጥረኛ ሰራኞቻችን ላይ የሚፈፀሙት አረመናዊ ድርጊት ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው፡፡ በስቃይ በትራቸው ህይወቷ ያለፈችውን እህታችንንት አስክሬን በክብር ከመላክ ይልቅ የሰውነት አካሏን እየበለቱ የሚያወጡ ናቸው። ግብረገብነት ይሌላቸው፣ ለማህበረሰብ የማያስቡ አረመናዊ በትራቸው የሚበረታ ከሊባኖሳውያን ዜጎች ምን መማር ይቻለናል?  ለዚያውም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን እንዴት ሊያስተምሩ ይችላሉ? እናም ዛሬ የመጡልንን ሊባኖሳዊያን አስተማሪዎች እንዴት እንመን! በቅርቡ ከማዳስካር ወደ ሊባኖስ ከሄዱ 85 ሰራተኞች  መካከል በአንዷ ላይ የፈፀሙት ግፍ የአገሪቱ መንግስት ን በ24 ሰዓታት ቀሪ ዜጎቹን ከሊባኖስ ለማስወጣት አስገድዶታል። በእኛ ኢትዮጵያውያኑ ቅጥረኞች ላይ ግን ለዓመታት በደል ሲፈፅሙ ከኖሩት ሊባኖሳውያን ዜጎቻችንን መታደግ ተስኖን መኖራችን እያንገበገበን ጭራሽ እነርሱኑ እንዲያስተምሩን የጋበዙልን እነማን ይሆኑ? እንደ እኔ በጥቅሉ ከሊባኖሳውያን መልካም አስተምህሮት ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከየዋህነትም በላይ ጅልነት ነው፡፡

ይልቁንም የአገራችን ኡለሞች ለሌሎች የተትረፈረፈ ዕውቀት አላቸው። ለምሳሌ በሳውዲ ታላላቅ ቦታዎች የማስተማር ልምድ ያካበቱ ታዋቂ ምሁራኖች ሞልተውናል፡፡ ከውጪ ማምጣቱ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘስ እነሱዳንና ግብፅ ለም እንደተዘነጉ በራሱ የሚገርም ትዝብትን ያተርፋል። ከእነዚህ ጎረቤት አገራት ምሁራን ቢመጡ በባህልም ሆነ በጂኦግራያዊ አቀማመጥ ተመሳሳይነት ስላላቸው ከኢትዮዽያውያን ሙስሊሞች ጋር የተሻለ መቀራረብና መተማመን ስለሚኖራቸው ጥሩ በተማርንባቸው ነበር። ከዚህም በላይ ለሀበሻ ያላቸውን ክብር ባየን ምንኛ መልካም ነበር እያልኩ ወደ አህባሾች ስልጠና መድረኮችና  አንደምታዎቻቸው ልሸጋገር፡፡

የስልጠና መድረኮቹን በወፍ በረር

የስልጠና መድረኮች (ወሃብያን) ለመዋጋት እንደተዘጋጁ የመነገሩ ጉዳይ ብዙሃኑን ግራ ያጋባ ከመሆኑም በላይ የቃሉ ምንነት እና የትኛዉን አካል ለማመላከት ጥቅም ላይ እንደዋለ ግልፅ አይደለም ። በመሰረቱ “ወሃብያ” እንደ አመለካከት ተይዞ ከሆነ ቃሉ ምን እንደሆነ ተናጋሪዎቹ በዉል የተገነዘቡት አይመስለኝም። በነገራችን ላይ ወሃብያ የመሀመድ ኢብኑ አብዱልወሃብ ስም ነዉ። ከ1703 እስከ 1791 እ.ኤ.አ ደዕያ በተባለችዉና በሳዑዲ አረቢያ አካባቢ የሚኖር የነበረ የአካባቢዉ ማህበረሰብ ሃይማኖታዊ መሪ የነበረ ግለሰብ መጠሪያ ስም እንጂ የሌላ ወካይና ገላጭ ቃል አለመሆኑን ሊታወቅ ይገባል። በወቅቱ እርሱ በሚኖርበት ዘመንና ቦታ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች ያካሂዱት የነበረዉን የጣዖት አምልኮ እንዲተዉ ያስተምርና ይታገል የነበረ ሰዉ ነዉ። ተዉሂድን የማስተማር እንቅስቃሴዉም ከፍተኛ የነበረና (መፅሃፍ በመፃፍ ጭምር ) ባደርገዉ የማስተማር ተሳትፎው ታዋቂነትን ያተረፈ ሰዉ እንደሆነ ከታሪክ ድርሳናት እንረዳለን። ከዚህ ዉጪ ግን በሌላዉ ላይ ጦር የሰበቀ ግለሰብ አልነበረም ። ከሞተ ሰዉና ጣኦት አምላኪነት ህብረተሰቡ እንዲላቀቅ ባካሄደዉ የማስተማር ዘመቻ ማንንም አልገደለም። በጥቅሉ ወሃብያ የሚለዉ መጠሪያ የዚህ ሰዉ ስም ከመሆን የዘለለ መገለጫ ሊኖረዉ እንደማይችል መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል ።

ሌላዉ በስልጠናዉ መድረኮች በተለይም በባህርዳር አካባቢ በተዘጋጁ መድረኮች ላይ በስፋት ወሃብያን እና የሳዑዲ ዓረቢያን ንጉሳዊ አገዛዝ እና ዜጎች ከ“ወሃብያ” ጋር የማስተሳሰር አዝማሚያዎች የመታየታቸዉ ጉዳይ ነዉ።

የሳዑዲ ዐረቢያ ህገ-መንግስት የተራቀቀዉ ቁረአንና ሃዲስን መሰረት አድርጎ እንጂ የወሃብያን ስርዓት መሰረት አያደርግም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወሃብያን ከአልቃኢዳ ጋር የማቆራኘት አዝማሚያ በስፋት ተንፀባርቆ ነበር። እዉነታዉ ግን አልቃኢዳ የራሱ ዓላማ ያለዉ አሸባሪና አጥቂ ቡድን ሲሆን ሳዑዲ አረቢያም በዚህ አጥቂ ድርጅት በተደጋጋሚ የተጎዳች ሀገር ሆና እናገኛታለን ። በአልቃኢዳ የፈንጂ ጥቃቶች ሳቢያ አያሌ ንፁሃን ዜጎቿ አጥታለች ። ሃቁ ይህ ሆኖ እያለ ግን ወሃብያን ከአልቃኢዳ ጋር ማቀላቀል ታሪካዊ ጥፋት ነዉ። የስልጠና መድረኩ መሪዎች ወይም አሰልጣኞች ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሳዑዲ አረቢያን እንደ ሃገርና እንደ ህዝብ ማዉገዛቸዉ በግልፅ ታይቷል። ይህ ምክንያቱ ደግሞ አንድና አንድ ነዉ። እሱም አብደላ አልሃረሪ ለሳዑዲ ትልቅ ጥላቻ ያለዉ ሰዉ ሰለነበር ነዉ። ጥላቻዉ የመነጨዉ ደግሞ ሳዑዲ ዐረቢያ በወቅቱ ሊባኖስ ከ17 ዓመት በኋላ በጧኢፍ ስምምነት መሰረት የእርስ በርስ የጎሳ ግጭቷ እንዲያቆምና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንባት ግንባር ቀደም ሚና በመጫወቷ ነዉ። አብደላ አልሃረሪ በወቅቱ ከጀርባዉ የነበረዉ የእስራኤልን ተልዕኮ ለማሳካት ይህ ሁኔታ አልፈቅድለት ስላለ ነው። በተጨማሪም ወደ ሠላም የመጡ የወቅቱ የሊባኖስ መሪዎች ስምምነቱን መቀበላቸዉ የሳዑዲ አረቢያን የሽምግልና ጥረት በበጎ ስለማይመለከተዉ ነበር።

ያም ሆነ ይህ በስልጠና መድረኮቹ ሳዑዲ ዓረቢያን እንደ አገርና እንደመንግስት ማዉገዙ በኢትዮ-ሳዑዲ የወደፊት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያ መጥፎ ጥላ የሚያጠላ መሆኑ አይቀሬ ነዉ። በተለይ እንደተወገዙ ከሰሙ በሳዑዲ የሚኖሩ ከግማሽ ሚሊየን ያላነሱ ዜጎቻችንን “ከአገሬ ይዉጡ……” ብትል፤ ተጎጂዎቹ እኛዉ ነን። በዚህ ደግሞ ሀገርም መንግስትም ይጎዳሉ። ስለዚህ ይህችን አገር ማስኮረፍ ሊያስከትል የሚችለዉ ችግር ምን ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ የተወሰደበት አይመስለኝም።

ከዚህም ሌላ ለስልጠና መድረኮቹ ማስፈፀሚያ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ መደረጉ እና ስልጠናዉ ከሚያስገኘዉ ወጤት ወይም ለዉጥ ጋር ሲነፃፀር ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ይመስላል ። መጅሊሳችን ለስልጠናዉ ይህን ያህል ገንዘብ ከመንግስት ተደጉሞ ጭምር እኔዳወጣ በሠፊዉ ይነገራል። ይህን ከማድረግ ይልቅ በየጊዜዉ ለስደት የሚዳረጉትን የአርብቶ አደር እና አርሶ አደር ልጆች በስደት በየበረሃዉ እየወደቁ ፣በየባህሩ እየሰመጡ ከሚያልቁ እነዚህን ዜጎቻችንን ለመቋቋም ወይም በተለያዩ የስራ ፈጠራ ፕሮጀክቶች እነዲሳተፉ ቢያደረግና፤ በዚህም ራሳቸዉን እና አገራቸዉን እንዲጠቅሙ ከመንግስት ጋር ተባብሮ ቢሰራ ምነኛ ባማረበት ነበር!

ከዉጪ ፖሊሲያችን አኳያ አሉታዊ ተፅዕኖዎች

ኢትዮጵያችን በተለይም በአፄዎች ዘመን ታራምድ የነበረዉ የዉጪ ግንኙነት ፖሊሲ ትኩረት ከካፒታሊዝም አገራት ጠንካራ ግንኙነትን መመስረት ላይ አትኩሯል። በተለይ ደግሞ በዘመነ ደርግ ከዓረብ አገሮች  ጋር ግንኙነታችን ሻክሮ የቆየና በተለያዩ መስኮች በትብብር አብሮ የመስራት ዕድሉ ዝግ ሆኖ የቆየበትን ሁኔታ እናስታዉሳለን። በአሁኑ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ግን ግንኙነታችን በአዲስ ምዕራፍ የሚቀጥልበትንና በጋራ የምንሰራበትን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ የዉጪ ግንኙነት ፖሊሲ ተቀርጾ ስራ ላይ ውሏል። በማንም አገር የዉስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ባለመግባት በጋራ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንንና ፍላጎታችን ዙሪያ ተቀራርበንና ተፈቃቅደን መስራት የምንችልበት መርህን በሚከተለዉ የወቅቱ የዉጪ ግንኙነት ፖሊሲያችን አማካኝነት በተለይ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በኢኮኖሚ፣ በልማቱና ኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በላቀ ደረጃ መጠቃቀም ይቻላል። እንዲሁም አገራችን ካላት የቆየ ኢስላማዊ ታሪካዊ አሻራዎች አንፃርም በቱሪዝም መስክ የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር ተችሏል። ይሁንና ይህ ግንኙነታችን ያልተዋጠላቸዉ አንዳንድ የዉጪና የዉስጥ ሃይሎች ጅምር ጥረቱን ለማኮላሸት ሲባዝኑ ይስተዋላሉ። ይህም በቅርቡ በተካሄደዉ አንዳንድ የአህባሽ የስልጠና መድረኮች ሳዑዲ አረቢያን የማዉገዝ አዝማሚያ በማንፀባረቅ የተገለፀ እዉነታ በመሆኑ ጉዳዩ እንደገና መጤን እንደሚገባዉ አመላክቷል።

“አላዋቂ ሳሚ……….ይለቀልቃል”

ከዚሁ ወቅታዊ አጀንዳ ጋር ተያያዥ ነጥብ ላንሳ …በማህበረ ቅዱሳን ሐመር መፅሄት ጥር 2002 ዳንኤል ክብረት በ1991 “አክራሪ እስልምናና ለኢትዮጵያ ያለዉ አደጋ ” እንዲሁም “አክራሪ እስልምናና የኢትዮዽያ ቤተክርስቲያን አስቸጋሪ ፈተና” በሚል በ1999 የፃፈዉ ፤ኤፍሬም እሸቱ እ.ኤ.አ ‹‹እስልምናና አክራሪነት በክርስቲያን ደሴት ኢትዮጵያ ላይ ያለዉ አደጋ›› በሚል በ2008 ከአሜሪካ የፃፈዉ  ፤ አባ ሳሙኤል ‹‹የሃይማኖት መቻቻል አለ የለም?›› በሚል ርዕስ በዝክረ ዘመን መፅሄት ላይ በ2000 ያሰፈሩት ፅሁፍ እና ሌሎችም መሰል ፅሁፎች ጀርባ ያሉት አንድምታዎች ሲታዩ ለሀገርና ለህዝብ የማይበጁ ከመሆናቸውም በላይ የእርስ በእርስ መቻቻልንና  መከባበርን የሚያጠለሹ ይዘቶች እንዳሏቸዉ እንረዳለን። ለዛሬዉም ወቅታዊ አደጋ ደጋፊና መንስኤ የሆኑት እነዚሁ የፀሃፍቱ መረጃዎች በትክክለኛ መረጃ ላይ አለመመስረታቸዉ እንዳለ ሆኖ ለኛ ለኢትዮጵያዉያን ህዝቦች የሃይማኖት መቻቻል እና መከባበር የማይፈይዱ የመሆናቸዉ ጉዳይ ጎልቶ ይታያል። በአጠቃላይ እስልምና ተግባሩ ከቁርኣንና ከሃዲስ በማያወላዳ መንገድ የተቀዳና ተፈፃሚነቱም ይህንኑ የተከተለ መሆኑ እየታወቀ፤ በዚህ መርህ መሰረት የአምልኮ፣ የአለባበስና ሌሎችም የህይወት እንቅስቃሴያቸውን የሚያደርጉትን ሙስሊሞች “ወሃብያ” በሚል መፈረጅ አግባብ ካለመሆኑም በላይ የሃይማኖት ነፃነትን መጋፋትና ሳይደርሱ መድረስን ያነገበ ሰላም አደፍራሽ አስተሳሰብ ነው። አደገኛ አስተሳሰብ! ኺዋሪጅ፣ አልቃኢዳና ወሃብያን አቀላቅሎና ትርጉማቸውን አዛብቶ የሚካሄደው ፍረጃ ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን ለመበጥበጥና ለመበጣጠስ ያቀዱ ዕኩይ ኅይሎችን ተልዕኮ ከመስበክ ያለፈ ፋይዳና አሳማኝ ምክኒያት የለውም። ለዚህም ነዉ “አላዋቂ ሳሚ… ይለቀልቃል” ያልኩት።

ምን ይጠበቅብናል?

መላዉ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ማህበረሰብ ጥንትም ሆነ ዛሬ ከማንም ጋር ጠብ የለዉም። ከሃይማኖት ተቋምም ጋር ቁርሾ የለዉም።ሊኖረዉም አይችልም። ከመንግስትም ጋር እንዲሁ! የኢህአዴግ መንግስት ሃይማኖቱን እንዲያራምድ ሕገመንግስታዊ ነፃነትና መብትን አጎናፅፎታል። ባህሉን፣ ልምዱን፣ ወጉን ኢስላማዊ መገለጫዎቹን እና ቅርሶቹን ተንከባክቦ እንዲይዝ ፣እንዲያቆይና ለትዉልድ እንዲያስተላልፍ ብሎም ለዓለም ማህበረሰብ እንዲያስተዋዉቅ ዕድሉንና መብቱን ሰጥቶታል ። ይህም ህገመንግስታዊ ዋስትናን አግኝቷል። የዜግነት ክብሩንና መብቱን ከሃይማኖት ነፃነቱ ጋር አረጋግጧል። እናም የኢህአዴግ ጠላት ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ከገዢዉ ፓርቲ (መንግስት) ጋር ተባባብሮ በጋራ አገራዊ ጉዳዩች ላይ እንደ ዜጋ የሚጠበቅበትን ድርሻ በላቀ ደረጃ እይተወጣ ይገኛል ። ይህ ህዝበ ሙስሊሙ ከመንግስት ጋር ያለዉ መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ እንዳይሸጋገር የሚያደናቅፉ ሃይሎችን ግን መንግስት በበሳል አመራር እና ዉሳኔ አሰጣጥ ልምዱ እንዲከታተላቸዉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖረው ሙስሊም በአፅንኦት እየጠየቀ  ይገኛል። እንደሌሎች እምነት ተከታይ የአገሪቱ ዜጎች ሁሉ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ በህገመንግስታዊ ስርአቱ የተሰጠዉን መብት መጠቀም ብቻ ሳይሆን፤ ሙስሊሙ ይህንን ያረጋገጠለትን ህገመንግስታዊ ስረዓት ይጠብቀዋል። ይንከባከበዋል። ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማክበርና በማስከበር ሂደቱም ከመንግስት ጎን ይሰለፋል። ይህንኑ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት አሳይቷል። ወደፊትም በዚሁ አቋም ከመንግስት እና ከህገመንግስታዊ ስርአቱ ህልዉና መጠበቅ ጋር ለመራመድ የሚተጋዉ ሙስሊም ማህበረሰብ ግን በሃይማኖቱ ጉዳይ ላይ የማንንም ጣልቃ ገብነት አይሻም። በህገመንግስቱ ከተደነገገዉ ዉጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ይቃወማል። መንግስት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወይም በሌሎች የዉጪና የዉስጥ ሃይሎች አለያም በፀረ-ኢስላም አቋም ላይ በሚገኙ ወገኖች ግፊት ወይም ጫና በሙስሊሙ ማህበረሰብ መንፈሳዊ አጀንዳ ዉስጥ ሊገባ አይገባዉም። በቅርቡ በአንዳንድ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ግን ሲገባ ተስተዉሏል። ይህ ሁኔታ ታዲያ በአገር ዉስጥም ሆነ በዉጪ የሚገኙ ኢትዪጵያዉያን ሙስሊሞችን ቅር ማሰኘቱ አልቀረም ። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ አሁንም መንግስታችን ሁኔታዉን በሰከነ መንገድ በማየት እንዲመረምረዉና መፍትሄ እንዲሻለት ፍፁም ሰላማዊ ጥያቄዉን ለመንግስታች በተለያየ መንገድ እያቀረበ ይገኛል።

ከሁሉም በላይ አገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ ያላትን ክብር በተለይም ከዓረቡ አለም ጋር ያላትን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ይህ ክስተት እንዳያጠለሸዉ ይሰጋል። ዛሬ የዓረቡ ዓለም “የዓለም 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ሙሰሊሞች ለሃገራችን ህዝቦች ባለዕዳ ናቸዉ” እስከማለት በደረሱበት ወቅት ከ1433 ዓመታት በፊት መቀበሏ በዓለም  እስልምና በነፃነት የኖረባትን ታሪካዊ ማዕረግና የመልካም እሴት ተምሳሌትነቷን የሚፈታተን አደጋ እንዳያጋጥም የብዙዎች ስጋት ነዉ፡፡ 50 ሺ አባላትን ከመላዉ አለም ያሰባሰበዉ ዓለም አቀፍ ሙስሊም ማህበረሰብ የአብደላ አልሃሪሪ የአህባሽ አመለካከት ከእስልምና መስረታዊ ህግጋት ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ዉድቅ ካደረገዉ ሰነባብቷል። ይህ ቡድን ግን ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞችን በአስተሳሰቡና አመለካከቱ ለማጥመቅ ፈቃድ አግኝቷል። እዚህ ላይ ቡድኑ ለምን ገባ አደልም ጥያቄዉ፤ “መጅሊስ ከመንግስት ጋር ተባብሮ ቡድኑ ስልጠና እንዲሰጥ ሁኔታዎች ለምን ተመቻቹለት?” ፤ “ይህን አመለካከት ለምን ተቀበሉ እንባላለን?፣ ህዝበ ሙስሊሙ ድህነትና ኋላቀርነት ከመንግስት ጋር ተባብሮ ለማስወገድ እየተጋ ባለበት ወቅት አንድነቱን የሚከፋፍል አመለካከት ካልተቀበልክ ለምን ይባላል?” የሚለው ነው የብዙዎቹ መሰረታዊ ጥያቄ! እናም መንግስትና ህዝበ ሙስሊሙን ለማራራቅ የሚሯሯጡ ሃይሎች ከእኩይ ድርጊታቸዉ ይታቀቡ ዘንድ የመንግስትን ትብብር እየጠየቁ የሚገኙት የብዙሃኑ ህዝበ ሙስሊሞች ጥያቄ ፍትሃዊና ፈጣን ምላሽ ከመንግስታችን እንደሚሰጠው ተስፋ በማድረግ ፅሁፌን እቋጫለሁ። ቸር ያሰማን፤ ሰላም!

AL-ISLAM 28

Posted: January 2, 2012 in ALL

Posted: November 2, 2011 in ALL

አክራሪው ማነው ?

Posted: October 9, 2011 in ትዝብት

አንዳንዴ በኢትዮጲያችን ውስጥ ለአንድ ሰሞን በተለይ ሀላፊነት ላይ ባሉ ሰዎች ዘንድ በተደጋጋሚ በሚዲያ የሚሰሙ ቃላቶች ይገርሙኛል ። አብዛኞቹ ልማትን ያማከሉ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ፖለቲካዊ መልእክት ያዘሉ ናቸው ። አንዳንዶቹ ደግሞ ከምንም ተነስተው ነገርን ለመጫር የሚደረጉ ናቸው ። የተወሰኑት ደግም ‘ ለምን ይሆን ! ደግሞ ምን ተፈጥሮ ይሆን ! ምን ታስቦ ይሆን !’ የሚያስብሉና ብዙሃኑን ግራ የሚያጋቡ ናቸው ።  ሰሞኑን የመጅሊሣችን ተጠሪ የሆኑት ሸህ አህመዲን ዐብዱላሂ በተደጋጋሚ የሚጠቀሟቸው ቃላት ምንጫቸውና መነሻቸው ምን እንደሆነ ሊገባኝ ስላልቻለ ነው ይህን ማንሣቴ ። ለኔ ብቻ አይደለም ለብዙዎቻችንም እንደማይገባ እርግጠኛ ነኝ ። ‘ አክራሪ ! አክራሪ ! ’  የሚለው ቃል ባልተለመደ መልኩ የሰሞነኛ ነጠላ ዜማ ሆኖብናል ። በዒድ ዋዜማ ፣ በሀረሩ ጉባኤ ፣  በልማት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት…  ይህ ቃል በተደጋጋሚ ተሰምቷል ። ‘ አክራሪ እይታ ያላቸው ፣ አክራሪ አመለካከት የተጠናወታቸው ….።’ ቃላቶቹ  ማን ላይ ይሆን የሚያተኩሩት ? ማንን ይሆን የሚመለከቱት ? ወደማን ይሆን የሚያነጣጥሩት  ።

‘ አድ ዲኑ አን ነሲሃ ’ “ ሃይማኖት ማለት መመካከር ነው ” ይላሉ ታላቁ ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ። ከዚህ በመነሣት በዛሬው መጣጥፌ ለመጅሊሣችን አንዳንድ ምክሮች ለማስተላለፍና የተወሰኑ ጥያቄዎችን ም ለመጠየቅ ወደድኩ ።

እንደሚታወቀው ህዝበ ሙስሊም ከአፄዎቹ ዘመን ጀምሮ እስከ ደርግ ድረስ በቀጠለው የረጅም አመታት ሥርኣት ብዙ ብዙ ተበድሏል ብዙም ተሰቃይቷል ። ለዘመናትም በገዛ ሀገሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲታይ ኖሯል ። የደርግን መውደቅ ተከትሎ በተገኘው ዲሞክራሲያዊ መሻሻል የሙስሊሞች ደስታ እጅግ ከፍተኛ ነበር ። የሃይማኖቶች እኩልነትና ነፃነት በህገ መንግስቱ ተረጋገጠ  ። ሙስሊሙ ማህበረሰብም ሆነ ሌላው እምነቱን በተመቸው መልኩ ማራመድ እንደሚችልና መንግስትም በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባም ታወጀ ። ሆኖም ግን ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዛሬም ድረስ በሃይማኖቱ ዘና ብሎ መኖር አልቻለም ። ‘ አልሀምዱሊላህ ምስጋና ለአላህ ። አሁን መተንፈስ ጀመርን ’ ብለን ከመተንፈስ አልፈን ገና መናገር ስንጀምር ‘ አትናገሩ ’ የሚል ተቃዋሚ ከሩቅ አይመጣም ። ህዝቡ ፈታ ብሎ እንዳይኖር ምክኒያት ከሆኑት ድርጅቶች መካከል አንዱ መጅሊስ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ። መጅሊሱ በተለይ ላለፉት አሥራ ምናምን አመታት ከህዝበ ሙስሊሙ ተነጥሎ ብቻውን ኖሯል ። አሁንም ይሀው አካሄዱ የተመቸው ይመስላል ። ‘ ወክያለሁ ’ የሚለውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ ሣይሆን ጥቂት በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን አመለካከት በመጋራት ወደ ጥፋት ጎዳና እየገተጓዘ ነው ። ወደ አስፈሪ መንገድም እየመራን ነው ። ለህዝቡ መሥራትና መከራከር ሲገባው በህዝቡ እየሠራ ነው ። ጥያቄዎችንና ማብራሪያዎችን ለሚጠይቁትም ‘ አክራሪ ! አሸባሪ ’ እያለ መወንጀል ሥራ ሆኗል ። በመሆኑም ህዝቡ ዛሬም ተደናግጦ ይጠይቃል ።  የአክራሪ ነገር መደጋገሙ እየሆነ ያለ ነገር ወይንስ ወደፊት ስሚሆን ነገር ለማስጠንቀቅ ነው ? ። በክልል ከተሞችም ሆነ በአዲሳ አበባ ነገር አላየንም እና ምን መጥቶብን ይሆን ?  መሪያችንስ ምን ታይቶአቸው ይሆን ! ። 

በነገራችን ላይ .. ደግሞም የአክራሪነት ትርጉሙ አልገባንም እኮ ! ። እንዲያው ትርጉሙ ምን ይሆን በአላህ ! ። ሂጃብ መልበስ ነው ?  ኒቃብ ማጥለቅ ይሆን ? ሱሪ ማሣጠር ነው ? ፂም ማሣደግ ነው ? ለኢስላም መመሪያዎች ትእዛዛትና ክልከላዎች እራስን ማስገዛት ነው ወይንስ ሌላ ? ። በርግጥ ትርጉሙ ይህ ከሆነ እስቲ ሁኔታዎችን እናነፃፅር ። ለምንድነው አድልዎ የሚደረገብን ! ለምንድነው በተመሣሣይ ሥራ የተለያየ ሥም የሚሠጠን ?? ። ሙስሊሞች ፂማቸውን ያሣድጋሉ ፤ አይሁዶችም ሆኑ ክርስቲያን ቄሶችም ያሣድጋሉ ። የኛ አክራሪነት ተብሎ ሲፈረጅ የነሱ ለምን ሃይማኖት ሆነ ! ። የኛ ሴቶች ሂጃብ ይለብሣሉ ፤ ሴቶቻቸውም ቤተክርስቲያን ሲሄዱም ሆነ መነኩሴዎቻቸውም ይሸፋፈናሉ ። የኛ ‘ አሸባሪነት ’ ለምን ተባለ የነሱ እንዴት ጨዋነት ሊባል ቻለ ! ። የምእራቧ ሴት ልጇን ለማሣደግ ብላ ከቤቷ ትውላለች ፤ በዚህን ጊዜ ጥሩ እናትና ሀላፊነቷን ለመወጣት ደፋ ቀና የምትል ጠንካራ ሴት እንደሆነች ይነገርላታል ። ሙስሊም ሴቶቻችን ግን በፈቃዳቸው እቤት ሲውሉ ልጆቻቸውን በሥርኣት ሲያሣድጉ በኢስላም ሴቶች ተበደሉ ተጨቆኑ ተብሎ የሚጮሀው ለምንድነው ! ። ሙስሊም ያልሆኑ ሴቶች ያሻቸውን ለብሰው ፤ ሲሻቸውም ከባህላችን ወጣ ባለ መልኩ እርቃናቸውን ሆነው ፤ በአፍንጫቸው ፣ በጆሮአቸው ፣ በእንብርታቸውም ጭምር ሎቲ አንጠልጥለው ዩኒቨርስቲ ግቢ ሲገቡ እያየን ነው ፤ የኛዎቹ ጨዋነትን የተከተለ የተረጋጋ አለባበስ ሲለብሱ ግቢ እንዳይገቡ የሚከለከሉት ለምንድነው ! ። አክራሪ አሸባሪ የሚባሉት ምነ አድርገው ነው ። ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች የጎደላቸውንና የተነፈጉትን ነገር ሲጠይቁ ‘ መብታቸውን ነው የጠየቁት ’ ይባላል ። እኛ ግን ለመብታችን ድምፃችን ከፍ ያደረግን እንደሆነ ለምን ‘ አሸባሪ ’ እንባላለን ! ። ብዙዎች አንድ ሙስሊም ያልሆነ ሰው ያጠፋ እንደሆነ ስለ ሰውየው እንጂ ስለሚከተለው እምነት ለመጠየቅ ግድ የላቸውም ። አንድ ስለ ሃይማኖቱ ምንም የማያውቅ ምግባረ ብልሹ የሆነ ሙስሊም ሲያጠፋ ግን ለምን ከሱ ይልቅ ሃይማኖቱ ይተቻል ። ለምንስ አጥፊው እያለ እምነቱና ተከታዮቹ  ይወነጀላሉ ! ።

 እኔን የምለው  …. በየአመቱ ወደ ዩኒቨርስቲ ከሚገቡ ተማሪዎች መካል 80% ያህሉ ሙስሊም ያልሆኑት ሆኖ ሣለ  ‘ ዩኒቨርስቲዎች የአክራሪዎች መፈልፈያ ሆነዋል ’ መባሉ ገረመኝ ። በዚህም ሰበብ ‘ የጀመዓ ሰላትና ኒቃብ ሊታገዱ ነው ’ መባሉ በእጅጉ አሣዘነኝ ። በከፍተኛ የመንግስት ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሙስሊም ተማሪዎች ከመብታቸው ውጭ ምን ጠየቁ ! ። ግዴታ የተደረገባቸውን ሰላት በጀመዓ የሰገዱት ማንን ረበሹ ! ጅልባብ የለበሱት የማንን መብት ተጋፉ ! ኒቃብ የለበሱት እራሣቸው ለበሱ እንጂ ሌላውን መቸ አለበሱ ? ። ለመታደል ሆኖ ነው እንጂ መጅሊሣችን ለሙስሊም ተማሪዎች መብት መከበር መከራከር ነበረበት ። ከኒቃብ ለባሾች ጎንም መሆን ነበረበት ። ጠንካራና የተማረውን ሙስሊም መውደድና ማስጠጋት ነበረበት ።

 ለመጅሊሣችን የምንለውና የምናሣስበው ‘  የተማረውና ወጣቱ ክፍል ጠቃሚነቱ ለሀገሩና ለእምነቱ ነውና  እንዳይጠሉ እንዳይገፉት ነው  ። በተለያየ አመለካከት ላይ ቢሆኑ እንኳ የላኢላሀ ኢለላህ ቤተሰቦች ናቸውና እንክብካቤ ይደረግላቸው ። በዩኒቨርስቲ የሚገኙ ሁሉም የእምነት ተከታዮች መጠጊያ አላቸው ። የቲም ሆነው የቀሩት የኛዎቹ ብቻ ናቸውና ለልጆቻችን አባት ሁኑልን ነው ። በጥቃቅን ምክኒያቶች ውክቢያ እየተፈጠረባቸው ነውና ለመንግስት ቅርብ እንደመሆንዎ ሁኔታውን ይጠይቁልን ነው ።

 እኔን ያሣዘነኝ …  የመንግስታችንም በመጅሊሱ ሥራ መተማመን ነው ።  የደነቀኝና ሲበዛ የገረመኝ ነገር ቢኖር .. ‘ አክራሪዎች ናቸው ’ ያላቸውን ወሃቢዮችን ‘ ለማጥፋት ’ መጅሊሱ የተከተለው መንገድ ነው ። ሀገራት ለእድገታቸው የሚጠቅሟቸውን ቁሣቁሶች ለማስገባት ወዲህ ወዲያ ሲሉ መጅሊሣችን ግን የሙስሊሙን አመለካከት ለመቀየር ዐቂዳን /እምነትን/ በሸቀጥ መልክ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት መሞከሩ መጅሊሣችን የዋህ ስለመሆኑ አመላካች ነው ። ሰዎቹ ደህና የሚባል አማካሪ የሌላቸው መሆኑንም ያወቅኩት አሁን ነው ። እንደው ‘ ሰው ሁሉ አክራሪ እየሆነብን ተቸገርን ’ የሚል ከሆነ ስጋቱ እንዴት ብሎ አህባሽ ለአመለካከቶች አማራጭ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ! ። ኪታቦቹን በነፃ ማደልስ መርዝ ከማደል በምን ይለያል ! ።   አህባሽ ሀገራችን መጥቶ ምን እንዲሠራልን ይሆን የተመረጠልን ! ። ሊያሣድገን ነው ሊያደድበን ! ሊያነቃን ነው ውይንስ ሊያጀዝበን ! ሊመራን ወይስ ገደል ሊከተን ! ። ሙስሊሞች ‘ ነቅተናልና እራሣችንን አንጥልም ፣ ፀድተናልና አንቆሽሽም ፣’ እያሉ ነው ።   ጥሩን በመጥፎ ፤ ውዱን ነገር በርካሽ ፤ ቀላሉን ሸሪዓ በውስብስብ አመለካከት ማን ይለውጣል !።

እኔ የምለው … ‘ በጎ ባህሌን ፣ ጥሩ እምነቴንና  መልካም እሴቶቼን  አልለቅም ’ ስላለ ብቻ ህዝቡ ለምን አክራሪ ይባላል  ። አላህን እንጂ አልፈራም ፤ ባእድ አምልኮ አልቀርብም ፤ ቀብር አላመልክም ፣ ጠንቋይ አልቀልብም ፣ ጫት አልቅምም ፣ ዝሙት አልፈፅምም ፤ እኩይ ነገር አልሠራም ፤ ጊዜዬን በአልባሌ ነገሮች አላጠፋም.. ስላለ ብቻ ሰው እንዴት በአክራሪነት ይፈረጃል ? ። ባንመርጠውም የሙስሊሙ ወኪል ነኝ ብሎ በሥማችን ቁጭ ያለው መጅሊሣችን ተረጋግተንና ዘና ብለን እንድንኖር እድል ይስጠን ። ባይጠቅመን እንኳ አይጉዳን ። እኛን መፈየድ ቢያቅተው አይበድለን ። ኢስላማዊ ማእከላት ለምን ይዘጋሉ ። ሚዲያዎች ለምን ይጨቆናሉ ። ጋዜጠኞች ለምን ይታሠራሉ ! ። በየክልሉ አመራር ላይ ያሉ የመጅሊስ ሰዎች የማይፈልጉትን አመለካከት ለምን በግድ ይጋታሉ ። እኮ ለምን ??

እኔ የምጠይቀው …. የታለ አክራሪውን አሣዩን !  የት ነው ያለው ይነገረን ። ከህዝብ ድብቅ የሆነ ነገር የታለ ! ‘ የትኛው ሰው ይሆን በጉልበት አስተሣሠቤን  ተቀበሉኝ ብሎ በሰው ላይ የፈረደው !  የትኛው አዲስ አንጃ ይሆን አመለካከቱን እንዲቀበሉ ብሎ  ህዝቦችን ያስገደደው ! የትኛው ሙስሊም ነው ሰይፍ ያነሣው ! የትኛው ነው ኢስላማዊ መንግስት ይቋቋምልን ብሎ የጠየቀው ! ’ ሀገራችን ውስጥ አዲስ የመጣ ነገር አላየንም ። ህዝቡ በሰላም እየኖረ ተረጋግቶ ነው ። ህገ መንግስታዊ መብቱን በመጠቀምም እምነቱን በነፃነት እየተገበረ ነው ። በመሃል ድንገት ተነስቶ የሌለ ነገር በመፍጠር መጅሊስ ለምን ይረብሸናል ።   ‘  አክራራ ! አክራሪ ’ እያሉ ሰውን ማደንቆር ምን ይባላል ። ከዚህ በላይ ሽብርስ የት ይኖራል ! ።

 

 

መግቢያ

የአህባሽ ጉዳይ በኢትየጲያችን አነጋጋሪ አጀንዳ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል ። በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንም ስለዚህ ጀመዓ ብዙ ብዙ ተብሏል ። አነጋጋሪነቱም ያለምክኒያት አይደለም ። ከአስተሣሠብ እስከ ሥነምግባር ፤ ከእምነት እስከ ማህበራዊ ኑሮ ግንኙነት በእጅጉ የወረደ አመለካከትና አስተምህሮ ያለው አህባሽ በህዝቡ መካከል ማረፊያ ቢያገኝ ሊያደርሰው የሚችለው ጥፋት ከፍተኛ ይሆናል የሚለው የብዙዎች ስጋት ነው ። አህባሽ እንከኖቹ ብዙ ናቸው ።  ትኩረቱና መሠረቱ ከተውሂድ ይልቅ ወደ  ሽርክ ( በአላህ ማጋራት ) እና ወደ ሸርክ የሚያደርሱ መንገዶች ያዘነበለ  ነው ፤ ጥርት ካለው የቁርኣንና የሀዲስ ትምህርት በበለጠ ወደ ፍልስፍና እና መሠረት አልባ ቂሣዎች (ትረካዎች) ያደላል ፤ ከፍቅርና ከመደጋገፍ ይልቅ በማህበረሰቡ መካከል ጥላቻን ፣ ምቀኝነትንና ውጥረትን ያራምዳል ፤  ከሱ ውጭ ያሉትን ሁሉ የማክፈር (ከእስልምና የማስወጣት) ፖሊሲውና ‘ ለመቻቻል ወኔ የከዳው ስብስብ ’ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ የአህባሽ ጀመዓን አደገኛነትና የአስተሣሣቡን መርዛማነት አጉልቶ ያሣያል ። በመሆኑም ይህ ጉዳይ እጅግ አሣሣቢ ነው ስላመንበት በዛሬው የአጀንዳ አምዳችን የተለያዩ መረጃዎችን በማገላበጥ ስለዚህ ጀመዓ ምንነት በሚከተለው መልኩ አጠናቅረናልና ተከተሉን ።

    የኋላ ታሪክ

ዛሬ የምናነሣት የዐብደላህ አልሀረሪ (አልሀበሺ) ጀመዓ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው ያላት ። በምድር ላይ የሃምሣ አመት እድሜ እንኳን አልሞላትም ። የተመረሠተችው በሊባኖስ ሲሆን መሥራቹም የኛው ሰው ናቸው ። ሙሉ ሥማቸው ዐብደላህ ኢብኑ ሙሀመድ አልሀረሪ (አልሀበሺ) ይባላል ። በሀረር ከተማ ከአደሬ ብሄረሰብ ነው የተወለዱት ።  አልሀበሺ የዘር ሀረጋቸው ከቁረይሽ ጎሣዎች አንዷ ከሆነችው ከበኒ ሸይባህ  እንደሚመዘዝ ይነገራል ። ተከታዮቻቸው እሣቸው ይዘው የመጡትን ዐቂዳ / እምነት / ታላቅነት ለማመልከት የዘራቸውን ታላቅነት ይጠቅሣሉ ። በሌላ በኩል ግን ይህንን ጉዳይ የማይጋሩ በርካቶች ናቸው ። ናቸው ቢባል እንኳ ከተከበረ ዘር መሆንንና መልካምነትን የሚያገናኛቸው ነገር አለመኖሩን በርካታ ምሣሌዎችን በመጥቀስ ማስረዳት ይቻላል ። የዚህ ኡመት ፈርዖውን በመባል የሚታወቀውና በነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ዘመን ዋና የኢስላም ጠላት የነበረው አቡጀህል ከቁረይሽ ጎሣ መሆኑን ልብ ይሏል ። በቁርኣን ከባድ እርግማን የወረደበት አቡለሀብም ቢሆን የነቢያችን ሰላላሁ ዐለይህ ወሠለም አጎት የነበረ ስለመሆኑ አንዘንጋ  ። ዐብደላህ አልሀበሺ በልጅነታቸው በሀረር ገጠራማ አካባቢዎች የዐረብኛ ቋንቋና የሻፊዒይን ፍቅሂ ተምረዋል ። ሌሎች ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንም ከተለያዩ መሻኢኮች ቀስመዋል ።

የማይጨበጠው አቋማቸው

ዐብደላህ አልሀበሺ ከወጣትነት እስከ ሽምግልና በዘለቀው የህይወት ዘመናቸው አንድ አይነት አቋም ይዘው ሲጓዙ አልተስተዋሉም ። ለበርካታ ጊዜያት በሱፊያ አመለካከቶችና መንገዶች ውስጥ ሲወጡና ሲገቡ ቆይተዋል ። ሀረር እያሉ ቃዲሪያ የሚባል ጠሪቃ መንገድ ተከታይ ነበሩ ። ወደ ጅማ ሲሄዱ ደግሞ ቅልጥ ያሉ ቲጃኒ እንደነበሩ ይነገራል ። ከዚህም በተጨማሪ በየጊዜው የሚፈፅሟቸው ድርጊቶች ለብዙዎች ግራ የሚያጋቡ ነበሩ ። ሼክ አህመድ አድደውለዊ ስለሣቸው ያዩትን ሲናገሩ ‘ይህ ሰው በአንድ ወቅት ጅማ ሄዶ ሲመለስ በቲጃኒ ጠሪቃ ላይ ተመስርቶ አላህን የሚያወሣበት መስገጃው ላይ ተቀምጦ በዙሪያው ስድስት ሲጃዳዎች አንጥፎ አየሁት ። ስለዚህ ሁኔታ ተጠይቆም አንደኛዋ ሲጃዳ ለነቢዩ ናት ፤ ሁለተኛዋ ደግሞ ለኢማም አህመድ አትቲጃኒ ስትሆን የቀሩት አራቱ ደግሞ አውራዱ (አላህን ማውሣቱ) ላይ ይገኛሉ ተብለው ለሚጠበቁት ለአራቱ ኸሊፋዎች እንደሆኑ ተናግሯል ።  አልሀበሺ ሀረር ተመልሰው ጥቂት እንደቆዩ ግን ይህን ጠሪቃ ተው ። ቲጃኒዎችንም ማክፈር ጀመሩ ። ወደ ሊባኖስ ሲሻገሩ ደግሞ የሪፋዒ ጠሪቃ ተከታይ እንደሆኑና ከሌሎች የሚሻለውም ይሀው መንገድ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር ። በሊባኖስ ቆይታቸው ጥመትና አልባሌ ነገሮች ከሞላባቸው ከተለያዩ የፍልስፍና መንገዶች የተለያዩ አመለካከቶች መቅዳትና መገልበጥ ያዙ ።  ውርሣቸውም ይህን ይመስላል  -  በኢማን / እምነት/ ጉዳይ ላይ ከኸዋርጆች (አፈንጋጮች) ጋር በማበር ሙስሊሞችን ማክፈር ጀመሩ ።  ጀህሚያ እና ሙዕተዚላ ከሚባሉ ጀመዓዎች ደግሞ ደግሞ የአላህን መልካም ሥሞችና ባህሪዎች በመቁረጥ አሊያም በመቀጠል ለቁርኣን አንቀፆች ያልሆነ ትርጉም መስጠትን ወረሡ ።  ከሺኣዎች ደግሞ እነ ሙዓዊያን እና ዐምር ኢብኑልዓስን ጨምሮ ታላላቅ ሰሃቦችን የመስደብ ትልቅ ወንጀል ተጋሩ ። ከአህለልኪታቦች ደግሞ በተወሱል ሰበብ መቃብር ለመቃብር አማላጅ ፍለጋ መንከራተትን በትምህርታቸው ውስጥ አካተቱ ። ሸኹ እንዲህ የተሠባጠረ አካሄድ የሚከተሉ  ከመሆናቸው የተነሣ  የሣቸው መንገድ  ይህ ነው ብሎ በግልፅ ለማስቀመጥ ይቸግራል ። 

አመለካከታቸው

ሸኽ ዐብደላህ አልሀበሺ ከትንሽነታቸው ጀምሮ በባህሪያቸው አስቸጋሪ ሰው እንደነበሩ ይነገርላቸዋል ። ትክክል ነኝ ብለው ባመኑበት ነገር ከሸኾቻቸውና አስተማሪዎቻቸው ጋር ክርክር በመውደድ ይታወቃሉ ።  በዚህም የተነሣ በየጊዜው ከሚያስተምሩዋቸው ሸኾች ጋር ውዝግብ ውስጥ ይገቡ ነበር  ። ሰላትን ማንንም ተከትሎ ለመስገድ ፈቃደኛ አይደሉም ። ከሰዎች ጋር ላለመስገድ ሲልም ሰላታቸውን ያዘገዩ ነበር ። ከዚህም በላይ ሰዎች በሰላትና በቂርኣት በጥንቃቄ እንዲጨናነቁ ያስገድዳሉ ።  የገዛ ሸኻቸውን ጭምር ተከትለው የማይሰግዱ ሲሆን ክስተቱም አንድን ሙስሊም ለማነወርና ለማክፈር ዳርዳርታውን የጀመሩበት ወቅት ነበር ። ላለመስገድ እንደምክኒያትነት ያቀርቡ የነበረውም ኢማማቸው በዐረቢኛ የፊደል አወጣጥ (መኻሪጀልሁሩፍ ) ላይ ችግር አለባቸው የሚል ነበር ።  በወቅቱ ከተማሪያቸው ይህን ያስተዋሉት ሸህም  ‘ ይህ ሰው ወደፊት የፊትና ሰው ( ሰዎች በሱ የተነሣ የሚወዛገቡበት )  ነው  የሚሆነው ።’ እስከማለት ደርሰዋል ። ዘግይቶም ቢሆን የሸኹ ትንበያ የሠመረ ይመስላል ።  ዛሬ ዓለማችን እሣቸው ባመጡትና ከአራቱም መዝሀብ ውጭ በሆነው አዲስ አመለካከት ችግር ውስጥ የገባች ስትሆን በዋናነት ደግሞ ያደጉባት ሀገር ሊባኖስ ትልቅ ፈተና ውስጥ ናት ። ሸሁ የዛሬ ሁለት አመት አካባቢ ይህችን ዓለም በሞት ቢሰናበቱም የለኮሱት ፊትና ግን ዛሬም ከሀገር ሀገር እየዘለለ ነው ። ሸኹና ተከታዮቻቸው ብዙ ክርስቲያኖች ሺዓዎችና የተለያዩ አልባሌ እምነት ተከታዮች በሚገኙባት በዚህች ሀገር እግራቸውን ሊያቆሙ የቻሉት  ለሱና ሰዎች ባላቸው ጥላቻ የተነሣ ከምእራባውያን ፣ ከሺዓዎችም ሆነ ከሌሎች የኢስላም ጠላቶች ከፍተኛ ድጋፍ ስለሚደረግላቸው  ነው ይባላል ።

ማክፈር … ትልቁ መፈክር

ዐብደላህ አልሀበሺ ለማንኛውም ‘ ይቃወመኛል አሊያም አመለካከቴን አይጋራም ’ ብለው ባመኑት ሰው ላይ  ረጅም ምላሣቸውን ለመልቀቅ  ወደኋላ  አይሉም ። እሣቸውም ሆኑ ተከታዮቻቸው አንድን ሰው ለማክፈር እጅግ ሲበዛ ችኩሎች ናቸው ። በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ ሱፊዮች እስከዛሬ ድረስ ሰውን ሲያከፍሩ አልተስተዋለም ። አሁን የአህባሽ አመለካከት ከመጣ ወዲህ ግን እነሱም ወደማክፈር ገብተዋል ። ዐብደላህ አልሀበሺ   ‘ አትተዓዉን ዐላ ነህይ ወልሙንከር ’ ( በመጥፎ ነገር ላይ መረዳዳት )  በሚለው ኪታባቸው ላይ እንደፃፉትም ከትላልቅ ዓሊሞች ውስጥ የሚያስቀሩት ጥቂቶችን ብቻ ነው  ። ኪታባቸው ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ተህዚር ! ተህዚር… ! ተጠንቀቁ ተጠንቀቁ .. ! በሚል ማስፈራሪያ የተሞላ ነው ። ካለፉትም ይሁን በህይወት ካሉት ዑለማኦች ፣ ዳዒዎችና የኢስላም ተንታኞች ውስጥ ሰዎች ሊሸሿቸው የሚገባቸውን አንድ በአንድ ይዘረዝራሉ ። ዓሊሞቹ የተናገሯቸውን  ቃላት በመምዘዝም  ‘ እገሌ በአንድ ወቅት  እንዲህ ብሏል እገሌም እንዲህ ብሏል … እያሉ እራሣቸውን የዚህች ዓለም ብቸኛ ነቢይ አድርገው የማስቀመጥ ያህል  ይፈርዳሉ ። ሲሻው ይሣደባሉ ፤ ካልሆነም ይራገማሉ ፤ ባስ ካለም ያከፍራሉ ። ስድባቸውን የሚጀምሩት ከታላቁ ሰሃባ ከሙዓዊያ ኢብኑ አቢሱፍያን ነው  ። ስለ ዐምር ኢብኑል ዓስና ስለ እናታችን ዓዒሻም የሚሉት አላቸው ።  ይህም ያለ አንዳች ኤዲቲንግ (ማስተካከያ) ከሺዓዎች የገለበጡት ቀጥተኛ የሆነ አቋማቸው እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል ። ከሰለፍ ዑለማኦች እነ ዳርሚይንና ኢብኑ ኹዘይማህን ወርፈዋቸዋል ።  የተውሂድ አቀንቃኙ ኢብኑ ተይሚያህ ዋና ጠላታቸው ሲሆኑ ‘ ካፍር (ከሀዲ) ፤ ሙርተድ (ከኢስላም ወደ ክህደት የተመለሠ )’ በማለት ይገልጿቸዋል ።  በተገኙበት ሁሉ ኪታቦቻቸው እንዲቃጠሉ አዘዋል ። የኢብኑ ተይሚያን ተማሪ ኢማም ኢብኑ አልቀይም አልጀውዚን  እና ታላቁን ሙፈሲር (የቁርኣን ተንታኝ) ኢብኑ ከሲርንም አክፍረዋል ። ኢማም ዘሀቢን ኸቢስ  (መጥፎ) ሲል ይዘልፏቸዋል ። ታላቁ የሀዲስ ሰው ሸይኸ አል አልባኒ ፣ የሳዑዲ ሙፍቲ የነበሩት ሸኽ ኢብኑ ባዝና ታላቁ ዓሊም ኢብኑ ዑሰይሚን እንዲሁም የወቅቱ የዓለም ሙስሊም ዑለማኦች ዋና ፀሃፊ የሆኑት ሸኽ ዶ/ር ዩሱፍ አል ቀርዳዊም በካፍርነት ከተፈረጁ መካከል ናቸው ።  ሰዎች እንዲጠነቀቋቸው ከፃፉባቸው ሌሎች ሰዎች መካከል ታዋቂው ዳዒ ዶክተር ዐምር ካሊድ ፣ ፈይሰል መውለዊ ፣ ፈትሂ የኩን የመሣሠሉት ሲገኙ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ምሁራን ይገኙባቸዋል ። የሱፊያው መሪ ሸኽ ሙሀመድ ሰዒድ አልቡጢ ውግዘቱ ተርፎአቸዋል ። ዶክተር ዛኪር ናይክና የፒስ ቲቪ ባልደረቦቹም በክህደት ከተወነጀሉት ውስጥ ናቸው  ። አልሀበሺ ታላቁን የፍቅሂ ሰው ሰይድ ሳቢቅን መጁሲ /እሣት አምላኪ/ ሲል ይገልጿቸዋል ። ሰይድ ቁጥብን ከመራገም አልፈው እሱንና ተከታዮቹን  በስቅላት በመግደሉ ለጀማል አብዱናስር ታላቅ አድናቆት አላቸው ።

የስደቱ ምክኒያት  

‘ አልሀበሺ አክጣኡሁ ወሹዙዙሁ /አልሀበሺ ስህተቶቹና ድልጠቶቹ / ’ የምትለውና በዐብዱረህማን አድ ድመሽቂያህ የተዘጋጀችው ትንሽ መፅሃፍ አንደምታትተው ከሆነ አልሀበሺ ከትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጰያ  ሸሽተው የወጡት በሀረር ሙስሊሞች መካከል ውዝግብ በማስነሣታቸው ነበር ። በወቅቱ የሀረር ገዠ ከነበሩት የሃይለሥላሴ አማች አንዳርጌ ጋር በመተባበር በሀረር የሚገኙ የቁርኣን ሂፍዝ ማዕከላትን ማስዘጋታቸውም ተነግሯል  ። ጊዜውም በ1940 ዓ.ል ነበር ። በወቅቱ ወደ ተውሂድ ጥሪ የሚያደርጉ ዑለማኦች በአልሀበሺ ውንጀላ ከፍተኛ መንገላታታ የደረሠባቸው ሲሆን በርካቶች ወደ ግብፅና ሳዑዲ ዐረቢያ በመሰደድ ህይወታቸውን ሲያተርፉ የተቀሩት ደግሞ እንዲታሰሩና በጨቋኙ መንግስት እንዲዋረዱ ተደርጓል ። ሰዎችንም የሚያሣስሩበት ዋና ምክኒያትም ዛሬም ተከታዮቹ እንደሚወነጅሉት ‘ ወሃቢያ ነው ’ በማለት ነበር ። ሆኖም ግን ኋላ ላይ ተነቅቶባቸው እራሣቸው የለኮሱት እሣት ሊፈጃቸው እንደሆነ ሲረዱ  የታሠሩና የተገደሉ ሰዎች ቤተሰቦችን በቀል በመፍራት ከሀጃጆች ጋር በመሆን በሶማሊያ  በኩል አድርገው ሣዑዲ ሊገቡ ችለዋል ። ሸሁ ቀጥለውም  ወደ ሀገረ ኢስራኤል ኋላም ወደ ሶሪያ በመሻገር በመጨረሻም ሊባኖስን ማረፊያቸው አደረጉ ።   በሊባኖስ ቆይታቸውም ዓሊም መስለው በመቅረባቸው ብዙዎች በሣቸው ተታለዋል ። መጀመሪያ አካባቢ የተለያዩ አንዳንድ መፅሃፎችን በማረም ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ ገቡ ። ቀጥሎም ለየት ያለ አዲስ አመለካከታቸውን ማስተዋወቅ ያዙ ። ተውሂድ ይዞ የነበረውን ህዝብም ወደኋላ አንሸራተቱ ፤ በፍቅር ይኖር በነበረው ማህበረሰብ መካከል ፍትናን በማሠራጨት ጥላቻን በመንዛታቸውም አንድነታቸው ተበተነ ።  ሀይላቸውም ተዳከመ ።

ቁጥራቸው ስንት ይሆን

በዓለም ላይ የአህባሽ ተከታዮች ቁጥር ከ250 ሺህ እንደማይበልጥ ይገመታል ። የዓለም ሙስሊሞች ቁጥር ወደ ሁለት ቢሊዮን የተጠጋ ሲሆን በነሱ እይታ ከነሱ ውጭ የሆነው ሙስሊም ሁሉ ካፍር በአላህ ያላመነ ከሀዲ ነው ማለት ነው ። እስልምናቸውም ትክክል ስላልሆነ እንደገና ሸሃዳ እንድይዙ ይመክራሉ ። አህባሾች በእምነት ጉዳይ ከሺዓዎች የሚጋሯቸው በርካታ አመለካከት ያሏቸው ሲሆን ህዝቡላህን ከመሣሠሉ በኢራን ከሚደገፍ ፓርቲም ትልቅ ድጋፍ ያገኛሉ ። የሱና ጀመዓዎችን ለመቃረን ሲሉ ብቻ ከጥመትና ከኩራፋት ጀመዓዎች ጋር ፍቅራቸው እጅግ የጠነከረ ነው ። መሪዎቻቸውም ሆኑ ተከታዮቻቸው በስሜት የሚነዱ ፣ ለጥቅም ያደሩ ፣ ሥነምግባርና ዘመናዊ እውቀት የጎደላቸው ናቸው ። የሚያንቀሳቅሷቸው ድብቅ የሆኑ የሙስሊሙ ጠላት እጆች እንዳሉባቸው የብዙዎች ግምት ነው ።

ሱፍያ ፣ አል አሽዐሪይ ፣  ኢማሙ ሻፊዒይና አህባሽ

አህባሾች ‘ ሱፊዮች ነን የኢማም አሽ ሻፍዒና የአሽዓሪይ መዝሀብ ተከታዮች ነን ቢሉም አመለካከታቸው በብዙ መልኩ ከነሱ የተለዩ ነው ። ሱፊዮች ሙስሊሙን ሲያከፍሩ በታሪክ አልታየም ። ‘ ቁርኣን የአላህ ንግግር አይደለም ’ አይሉም ። ከመካና መዲና ኢማሞች ኋላ እንዳይሰገድም ብይን አያስተላልፉም ። ከካፍሮች (ከሀዲያን ) ጋር አብረውም ሙስሊሙን አይበድሉም ።  ከነቢዩ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሰሃቦች አንዱን እንኳ አይሰድቡም ። እነሱ ‘ እንከተላቸዋለን ’ የሚሏቸው ኢማሙ ሻፊዒይም ከአካሄዳቸው ፍፁም የጠሩ ናቸው ።  ኢማሙ በቀደምት ሰሃቦች መካከል ስለተፈጠረው ልዩነት ደፍረውና አፋቸውና ሞልተው ለመናገር አላህን ይፈራሉ ፤ ኢማሙ ሻፊዒይ  ‘ ያች በርግጥም ትልቅ ፈተና ናት ። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ከሷ እጃችንን  አጥርቶልናል ። ታዲያ ምላሣችንን ማጥራት አይጠበቅብንም ’ ሲሉ በቀደምት ሰሃቦች ውስጥ የተከሰተውን ነገር ከመተንተን ይቆጠባሉ ።  ኢማሙ ሻፊዒይ ሪባን /ወለድን / ም ሆነ ሰው ማጭበርበርን አይፈቅዱም ፣  ዘካን ከእስልምና አላስወጡም ፣ ለአላህ ባህሪያት ያለትርጉማቸው ትርጉም አልሠጡም ።

ዋና ዋና አመለካከት

v  ቁርኣን የመልአኩ ጅብሪል እንጂ የአላህ ንግግር አይደለም ይላሉ ። ቁርኣን የአላህ ንግግር ስለመሆኑ የሙስሊሞች ሁሉ እምነት ነው ።

v  በነሱ ጥላ ሥር ያልተጠለለውን ማንኛውንም ሙስሊም ሁሉ ካፊር ነው ይላሉ ። እውነተኛ ሙስሊም ማለት የነሱን አካሄድ የተከተለ አመለካከታቸውን የተጋራ ነው ። ከሀዲ ማለትም ከነሱ መንገድ የወጣ ነው ። አመለካከታቸውን ያልተቀበለውን ሙስሊም ስለሚያከፍሩ ተከትለውት አይሰግዱም ። ማክፈር በነሱ ዘንድ እጅግ ቀላል ነገር ነው ።   አንድ ካፊር ያልሆነውን ሙስሊም  ወንድሙን ካፊር ያለ ሰው ንግግሩ ወደሱ ተመላሽ እንደምትሆን ነበያችን አስተምረውናል ።

v  ‘ የሀረም ( የመካና መዲና ) ኢማሞችን ተከትሎ መስገድ ሀራም ነው’ ይላሉ ። ለሀጅ የሚሄድ ሰው እነሱን ተከትሎ መስገድ የለበትም ቢሰግድም ሰላቱ ትክክል አይደለም ብለው ያምናሉ ። ኢማማቸው አልሀበሺ ይህንን ያደረጉ እንደሆነ ደግመው እንዲሰግዱ ያዛቸዋል ። ለምን ቢባል በነሱ አመለካከት የሀረም ኢማሞች  ከሀዲዎች ናቸውና ነው  ። በዚህ አይነት በርካቶችን  የሀረም ተስግዶ የሚገኘውን ከፍተኛ አጅር አሣጥተዋል ።

v  የአላህን መልካም ባህሪያትና ሥሞች መካዳቸው ሌላው ነው ። አላህ ስለራሱ የተናገራቸውን ነገሮች ትርጉሙን በማጣመም ይተረጉማሉ ። ሲሻቸው ይቀንሣሉ ባሰኛቸውም ጊዜ ይጨምራሉ ። ቀደምት ሰለፎችና በተዋረድ እነሱን የሚከተሉ ሙስሊሞች ግን አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ስለራሱ በተናገረው መልኩ ያምናሉ ። እርሱ ለራሱ ያፀናውንም ባህሪ በሚገባው መልኩ ያፀናሉ ።

v  ሀጃቸውን ለማስፈፀም መቃብር አካባቢ ይመላለሣሉ ። ሙታኖች ሰዎችን ይረዳሉ ፣ ያግዛሉ ፣ ከጭንቅም ያላቅቃሉ የሚል እምነት አላቸው ። ከዚህም የተነሣ የአላህን በር ችላ በማለት ውሎአቸውን ደሪህ ካባቢ ያደርጋሉ ።  የአላህ ወሊዮች ከመቃብር ወጥተው የሰውን ጉዳይ ፈፅመው የመመለስ ብቃት አላቸው የሚል እምነት አላቸው ። ከአላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ሥምም በላይ የወሊዮቹ ሥም ሲጠራ ይበረግጋሉ ።

v  በዲን ውስጥ አዲስ ፈጠራን /ቢድዓን/ ያበረታታሉ ። ‘ መልካም ነገር እስከሆነ ድረስ ቢጨመርበት ግድ የለውም ’ በማለት ከሃይማኖት አስተምህሮ ውጭ የሆኑ ነገሮችን ይጨማምራሉ ። በዚህም የተነሣ አምልኮአዊ ተግባራቶቻቸው ከነቢዩ ሱናዎች ይልቅ በሌሎች መጤ ፈጠራዎች የተጥለቀለቁ ናቸው ።

v  ኢማን ማለት የውስጥ እምነት ነው በሥራ ባይገለፅም ችግር የለውም የሚል አቋም አላቸው ። በመሆኑም በሸሪዓ ህግጋት ለመሥራት የተሠላቹ ናቸው ። ለሀላል ሀራሙም ነገር ግድ የላቸውም ። ይህም በመሆኑ በምድር ላይ የአላህ ህግ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚፈልጉ በእጅጉ ይደግፏቸዋል ። ትክክለኞቹ ሙስሊሞች ግን ኢማን ማለት በቀልብ ውስጥ የሰረፀና በተግባርም የሚረጋገጥ ጉዳይ እንደሆነ ያምናሉ ።

v  ከአራተኛው ኸሊፋ ዐሊ ኢብኑ አቢጣሊብ ጋር በሀሣብ የተለያዩትን ሰሃቦችን እነ ሙዓዊያን እና ዐምር ኢብን አልዓስን ‘ ከአላህ ተእዛዝ የወጡ ናቸው ’ በማለት ይወርፏቸዋል ። ይህም የሺዓን አመለካከት የሚጋሩ መሆናቸውን አመላካች ነው ። በሊባኖስም ከሺዓዎች ጋር በመተባበር የሱና ጀመዓዎችን ሲያሣድዱ ይስተዋላል ።

v  አልሀበሺና ተከታዮቻቸው ከአመለካከታቸው ውጭ የሆኑትን ሙስሊሞች በመጥላት በመመቅኘትና እንዲሁም ሰሃቦች በመዳፈርና በመሣደብ ይታወቃሉ ።  ይህም በመሆኑ በሊባኖስ ውስጥ ተስማምቶ ለመኖር የማያመች ወጣ ያለ የቁጣ ባህሪ ያለው ሰው ካጋጠመ የአል ሀበሺ ተከታይ እንደሆነ ይገመታል ።  በሀገራችንም ውስጥ የምናየውም ሥራቸው ሰዎች ያላሉትን አሉ በማለት ትናንሹን ጉዳይ በማካበድ አንዳቸውን በሌሎች ላይ በማነሣሣት ነው ።

ከአስገራሚ ፈትዋዎቻቸው

  • በነጃሣ መስገድ ችግር የለውም ።
  • ወለድ መብላት ይበቃል ።
  • ሙስሊም ካልሆነ /ካፍር/ ጋር ቁማር ተጫውቶ መብላቱ ችግር የለም ። ችግር እስካልተፈራ ድረስ ።
  • ሴትን ልጅ በተደጋጋሚ ማየቱ ነው እንጂ የሚከለከለው በመጀመሪያ እይታ ለረጅም  ጊዜ ማየቱ ይበቃል ።
  • ሴት ልጅ በየትኛውም ጊዜ ያለባሏ ፈቃድ ሽቶ ተቀብታና ተኳኩላ መውጣት ትችላለች ።
  • ኢክቲላጥ /የሴቶችና ወንዶች ቅልቅል/ ችግር የለውም ። ለዚህም ሲባል ተከታዮቻቸው የሆኑ ወንድና ሴቶች ተቀላቅለው ይጨፍራሉ ።
  • ሙስሊም ወዳልሆኑ ሀገሮች የሚሄድ ሰው ችግር ይገጥመኛል ብሎ የሚፈራ ከሆነ መስቀል ማንጠልጠል ይችላል ።
  • ዘካ በወርቅና ብር እንጂ በወረቀት ገንዘብ ግዴታ አይሆንም ።
  • ሆን ብሎ መዘግየትና መስነፍ ችግር የለውም ። ለምሣሌ ጁሙዓና ጀመዓ ላለመምጣት የፈለገ ሰው ነጭ ሽንኩርት መብላት ይችላል ።
  • መኻሪጀልሁሩፍ /የዐረብኛ ቃላትን በትክክል ማንበብ ማይችሉ/ አሰጋጆችን ተከትሎ መስገድ አይበቃም ።
  • ለሴት ልጅ ከላይ ሂጃብ እስከለበሠች ድረስ ከታች ጠባብ ጂንስ ብትለብስም  ችግር የለውም ።
  • በአንድ ወቅት በአህባሽ ብይን የተነሣ በአሜሪካና ካናዳ የሚገኙ ሙስሊሞች ከከዕባ አቅጣጫ 90 ድግሪ ያህል ዞረው ሰግደው ነበር ።

ይህ ነው እንግዲህ ከእስልምና አስተምህሮ ወጣ ያለው ጥፋታቸውና አስቀያሚ አካሄዳቸው ። ልብ ያለው ልብ ይበል ።

 አደገኝነታቸው

የአህባሽ አመለካከት ወደ አንድ ሀገር አይደርስም የሚከተሉት ነጥቦች ቢከተሉት እንጂ

  • የሰዎች ለሰዎች ማህበራዊ ግንኙነት ይበላሻል ፣ የሙስሊሙ አንድነት አደጋ ውስጥ ይገባል ፣ ሽኩቻ ጥላቻና ውጥረት በመካከላቸው ይነግሣል ። ሙስሊሞች መሣቂያ መሣለቂያ ይሆናሉ ።
  • በምእመናን መካከል መተሣብና መተዛዘን ይጠፋል ፣ አሉባልታና የውሸት ወሬ ይስፋፋል ። 
  • ከሱና ይልቅ ቢድዓ ቦታ ያገኛል ፣ ከቁርንና ሀዲስ በበለጠ መሠረተ ቢስ ታሪኮችና ትረካዎች /ቂሳዎች/ ይገናሉ ፣ ከታላቁ ነቢይ ሥም በላይ የወሊዮችና የሸሆች ሥሞች ይዘወተራሉ ። የአላህ የአንድነት ትምህርት ይሸረሸራል ሽርክና ወደ ሽርክ የሚያደርሱ መንገዶች ክፍት ይሆናሉ ፤
  • ተውሂድ በሽርክ ይተካል ፣ ንቃት በመሃይምነት ይተካል ፣ ብስለት በስሜታዊነት ፣ እዝነት በጭካኔ  ፣ መተማመን በጥርጣሬ ፣ መቻቻል በብጥብጥ ይተካል ፣ ሚዛናዊነት በአክራሪነት ፣ አርቆ አስተዋይነት በችኩልነት ይተካል ። ከዚህም ባለፈ ሂጃብ በሱሪ ይተካል ፣ ቁርኣን በተለያዩ ሀድራዎችና ሙዚቃዎች ይተካል ።
  • መናፍቃን ቦታ ያገኛሉ ፣ የሱና ሰዎች ይጠላሉ ፣ በኢስላም ሀግጋት ለመሥራት ደፋ ቀና የሚሉ ‘ አክራሪ ፣ አሸባሪ ’ ይባላሉ።

 አለማቀፍ ዓሊሞች ምን ይላሉ

ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ከሱፊያም ሆነ ከሌላ ጀመዓ የሆኑ የአራቱ መዝሀብ አለማቀፍ እውቅና ያላቸው የዘመናችን ዓሊሞች ከዚህ ጀመዓ በማስጠንቀቅ ረገድ አንድ ሆነዋል ።

v  አብዛኛዉ ዓሊሞቹ በሱፊያ መዝሀብ ላይ የሚገኙት የግብፁ ታላቁ ኢስላማዊ ተቋም አል አዝሀር እነሱን አላውቃቸውም ብሏል ። ጠማሞች ስለመሆናቸውም በተደጋጋሚ ገልጿል ።  የአዝሀር ዩኒቨርስቲ ዳይሬክተር አህመድ ዑመር ሃሽም ‘ ይህ ጀመዓ በቁርኣንም ሆነ በሀዲስ የማይመራ ነው’ ብለውታል ።

v  የሊባኖሱ ሙፍቲ ሸኽ ኻሊድ ሀሠን ከሀገሪቱ መንግስት ርእሰ ብሄር ረሺድ ከራሚ በአንድ ወቅት ዐብደላህ አልሀረሪ ከሀገር ወጥቶ በነበረበት ወቅት በሱና ሰዎች ላይ በሚያደርገው አደገኛ አካሄድ የተነሣ ወደ ሀገር ወስጥ እንዲገባ እንዳይፈቀድለት ጠይቀው የነበረ ሲሆን ለጥቂት ጊዜ ታግዶ ነገር ግን በተለያዩ ምእራባውያን ሀገራት ግፊት የተነሣ ሊገባ ችሏል ።

v  የግብፁ ሙፍቲ ዶክተር ዐሊ ጁሙዓ  ‘ ሥሙ ዐብዱላህ አልሀረሪ አልሀበሺ የሚባል ሰውየመሠረታት ይህች ጀመዓ ውስጣዊና ውጫዊ ገፅታም አላት ። ውጫዊ ገፅታዋን ስናይ በፍቅሂ የሻፊዒይ መዝሀብ ተከታይ ፣ በዐቂዳ ደግሞ አሽዐሪን ይመስላሉ ። ውስጣዊ ተልእኮዋ ግን ያላግባብ ሙስሊሞችን ማክፈር፣ ምእመናን ያላግባብ መወንጀልና በሀዝቦች መካከልል ውጥረትና ውዠንብር መፍጠር ነው ። ለዱኒያዊ ጥቅም ሲሉም ለኢስላም ጠላቶች ይሠራሉ ። ብለዋል ።

v  በአውሮፓ የሙስሊም ኮሙኒቲ ሙፍቲ የሆኑት ዶክተር ፈይሰል መውለዊ ‘ የዐብደላህ አልሀረሪ ተከታዮች የሆኑት አህባሾች በጥቃቅን ነገሮች ሙስሊሙን ዑለማ የሚያከፍሩ ፤ አብዛኞቹ የሰለፍ ዑለማኦች የማይጋሯቸው የሆኑ የራሣቸው የሆነ አመለካከት /ዐቂዳ / ያላቸው ቡድኖች ናቸው ። ከሸኻቸው ውጭ ስለማይቀበሉ ከነሱ ጋር መነጋገር ጥቅም የለውም ። ከነሱ ጋር ላለመከራከር መስጅዳቸውን መሸሽ ይገባል ። ። እነሱ ከነሱ ውጭ የሆነውን ‘ ከሀዲ ነው ከነሱ በኋላ መስገድ አይበቃም ’ ብለው ቢያምኑም እኛ ግን ሙስሊሞች እንደሆኑና ከነሱ ጋርም ሆነ ተከትለዋቸው መስገዱ ይበቃል የሚል እምነት አለን  ።

v  የዓለም ሙስሊም ዑላማኦች ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ሼከ ዩሱፍ አልቀረዷዊም ‘ እነሱ የሚወክሉት የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል ብቻ ነው ። የሙስሊሙን  የጋራ አቋም /ኢጅማዕ/ በመጣል ተለይተው የወጡ ናቸው ። የሙስሊም ዑላማኦችን አክፍረዋል ። አህባሾች በጥመት ውስጥም በጣም የሰጠሙ ናቸው ። ኢማም ዘሀቢን ፣ ኢብኑ ተይሚያን ፣ ኢብኑልቀይምን ፣  ኢማም ገዛሊን ፣ ኢብኑ ዐብዱልወሃብን ፣ ኢብኑ ባዝን ፣ ሰይድ ቁጥብን  አንዱንም ሣይተው  አክፍረዋል ። መሃይማን ብቻ ሣይሆኑ ድርብ ድርብርብ መሃይሞች ናቸው ። ሁኔታቸው አላህ እንዳለው ነው “  ሰዎች እንዳመኑት እመኑ በተባሉ ጊዜ ሞኞች እንዳመኑት እናምናለን እንዴ! ” ይላሉ  ።

v  የሶሪያው የሱፊያ ዓሊም የሆኑት ዶክተር ሙሀመድ ሰዒድ አልቡጢም ‘በበይሩት ዐብደላህ አልሀረሪ የሚባል ኢማም ያላቸው አህባሾች  ወሃቢያን ተከትሎ መስገድ አይበቃም ፣ ኢብኑ ተይሚያ ካፊር ነው ይላሉ ። በመሠረቱ ወሃቢን ተከትሎ መስገድ ሀራም አይደለም ። ተከትሎ የሰገደም ሰላቱ ትክክል ናት ። አንድን  ሙስሊም ማክፈር ይበቃም ሲሞት በኩፍር ላይ ሆኖ ስለመሞቱ ማረጋገጫ እስካልተገኘ ድረስ ። ስለሷ የምታነሱልኝ ጀመዓ ብዙ ሙስሊሞችን ያከፍራሉ ። ሙተወሊ ሸዕራዊን ቀርዷዊን እኔንም ያከፍራሉ ። ምናልባት ሙስሊሞች እነሱ ብቻ ሣይሆኑ አይቀሩም ።’ ብለዋል ።

v  በሊባኖስ የሙስሊም ጀመዓዎች ተጠሪ የሆኑት ፈትሂ የኩን ‘ ዐብደላህ አልሀረሪም ሆነ ድርጅቶቹ ቀደምት ሰለፎችና የዚህ ኡመት ሚዛናዊ አመለካከት ያላቸው ምሁራን የጋራ አቋም የያዙበትን ነገር የሚቃረኑ ናቸው ።’ ብለዋል ።

v  በኢስላማዊ ብይኖች የበላይ የሆነው የሰኡዲ ቋሚ የሆነው የእውቀትና የፈትዋ ኮሚቴ በአንድ ወቅት  ‘ ዐብደላህ አልሀረሪ ኢስላምን አገለገለ ወይንስ አወደመው ? ’ ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ  እንዲህ በማለት መልስ ሰጥተዋል ። ‘ በሥም ተጠቃሹ እጅግ መጥፎ ሰው ነው ።  በዘመኑ ካሉ የቢድዓና የጥመት መሪዎችም አንዱ ነው ። እሱም ሆነ ተከታዮቹ ሆንብሎ ነቢያችን ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም ሰሃቦችና ታቢዒዮች ያስተላለፉልን የሙስሊሞችን ቀደምት አመለካከት /ዐቂዳ / ለማጥፋት ቆርጦ የተነሣ ሰው ነው ። በፍቅሂ ዙሪያ የራሣቸው የሆነ አካሄድ አዘጋጅተዋል ከቁርኣንም ሆነ ከሱና ሰንሰለት በሌላቸው ለየት ባሉ እና በዘቀጡ አመለካከቶች የተሞሉ ናቸው ። በዐቂዳና በሥራ በኩል ከፍተኛ የሆነ ችግር አለባቸው ። የዚህን ኡማ ታላላቅ መሪዎች በማነወርም ይታወቃሉ ። ሁሉንም ሙስሊሞች ከነኚህ ጠማማ እና የተንሸራተተ ጀመዓ እንዲሁም ወጣ ካለ አመለካከታቸው እንዲጠነቀቁ እንመክራለን ።’ ብለዋል ። 

v  ታላቁ የሀዲስ ሰው ሼኽ ሙሀመድ ናስረዲን አል አልባኒም ‘ አህባሾች የዐብደላህ አልሀረሪ ተከታዮች ናቸው ። አመለካከታቸው በአጉል ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ሲሆን ቁርኣንና ሀዲስን በዐቅላቸው በመመራመር እንጂ በሰለፎች ግንዛቤ ላይ አይረዱም ።

ተጠቃሽ ምንጮች

بغية الطالب للشبخ عبد الله الهرري

الحبشي أخطاءه وشذوذه عبد الرحمن الدمشقيه

صربح البيان للشبخ عبد الله الهرري

فرقة الأحباش د علي الشهراني

Antihabashis.com,

alsunnah. org

qaradawi.net

Bouti.com